ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ የምክክር ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ቀርጾ ይፋ ማድረግና ጉባዔውን ለመጥራት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 23/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ቀርጾ ይፋ ማድረግና ጉባዔውን ለመጥራት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

ወደዚሁ ወሳኝ ምዕራፍ ለመሸጋገር መከናወን ያለባቸው ወሳኝ ቀሪ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ''የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት'' በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኮሚሽኑ ምክክሩ ሁሉን አሳታፊና አካታች ለማድረግ ለተሳታፊ ልየታ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣የሃይማኖት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ ተቋማትና ማህበራትን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም መንግሥትን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ማካተትና ማሳተፍ መቻሉም ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰንም የዳያስፖራ ወገኖችም በሂደቱ እንዲሳተፉ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።

ኮሚሽኑ አሁን ላይ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ቀርጾ ይፋ ማድረግና ጉባዔውን ለመጥራት ጫፍ ላይ መድረሱን አስታውቀው፤ ለዚህም ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል።


 

ወደዚሁ ወሳኝ ምዕራፍ ለመሸጋገር መከናወን ያለባቸው ወሳኝ ቀሪ ተግባራት አሉ ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ የትግራይ ክልል ሕዝብና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አጀንዳቸውን የሚሰጡበትና በምክክር ጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ከመሳተፍ የታቀቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሂደቱ እንዲመጡ ለማድረግ ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ ማስፈለጉንም አንስተዋል።

በተጨማሪም መሳሪያ አንግበው የሚቀሳቀሱ ቡድኖችም ያሏቸውን አጀንዳዎች ወደ ምክክሩ አምጥተው መሳተፋቸው ለምክክሩ ሂደት ውጤታማነት ተጨማሪ አቅም በመሆኑ ልዩ ጥረት አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል።

በመድረኩ የተገኙ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መፍትሔ በማፍለቅ ረገድ የካበተ ልምድ ያላቸው በመሆን ቀሪ ስራዎች እንዲሳኩ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም