ቀጥታ፡

ብልህ ከችግር ይማራል!!

ብልህ ከደረሰበት ችግር ይማራል!! 

በማሙሽ ጋረደው 

ገራድ ተስፋዬ ተፈራ ትውልድና እድገታቸው በሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ ቃልሻ ቀበሌ ሲሆን በ1999 ዓ.ም በህገ ወጥ መንገድ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ገንዘብ ለማግኘትና የመለውጥ ህልማቸውን ለማሳካት በሚል ሩቅ አስበው የጀመሩት ህገ ወጥ ጉዞ መዳረሻውን እስር ቤት አደረገው። ይህም ሁኔታ ''ሩቅ አሳቢ-ቅርብ አዳሪ'' አደረጋቸው።

በባዕድ አገር በነበራቸው የ2 ዓመት የእስር ቤት ቆይታም የምግብ እጦትን ጨምሮ አካላዊ ጥቃትና ጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም የተለያዩ ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶችን እንዳስተናገዱ ይናገራሉ።


 

ይህም አልበቃ ብሎ ከአካባቢው በህገወጥ መንገድ የሚሰደዱ ወጣቶችን ጉልበት በመጠቀም ሰፋፊ እርሻዎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ የጉልበት ብዝበዛ ይፈፀምባቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።

ብልህ ከደረሰበት ችግር ይማራል! የሚሉት ገራድ ተስፋዬ ሩቅ ሳይጓዙ፣ ገንዘብ ሳያወጡ ሰርተው መለወጥ የሚችሉበትን አካባቢያቸውን ፀጋ ሳያማትሩ ስደት መሄዳቸው ቁጭት ፈጥሮባቸው ነበር፡፡

ይህም በሀገራቸው እንኳንስ የለማን መሬት ይቅርና የተቦረቦረ መሬትን አልምቶ ጉልበትንና ጊዜን በአግባቡ ተጠቅሞ ለስኬት መብቃት እንደሚቻል ከእስር ቤት ቆይታቸው ተምረው ከእስር እንደተፈቱም ወዲያውኑ ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በ2001 ዓ.ም ወደ ሀገር ቤት እንደተመለሱም  በማህበር ተደራጅተው ከመንግሥት ባገኙት 70 ሺህ ብር ብድር በእንስሳት እርባታ ላይ ለመሰማራት 4 የወተት ከብቶችን ገዝተው የእርባታ ስራ መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡ 


 

በዚህም የዞኑ አስተዳደር የሰጣቸውን መሬት አልምተው የእንስሳት እርባታውን አስፋፍተው መስራት ጀመሩ፡፡ አሁን ላይ የወተት ላሞቹን ቁጥር 37 በማድረስ የወተት ምርታማነታቸው አድጎ ከቤት ፍጆታ አልፎ ለሆሳዕና ከተማና አካባቢው በቀን ከ670 ሊትር በላይ ወተት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

ለ40 ወጣቶችም ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ከመፍጠራቸውም ባሻገር የተለያዩ የጭነትና የስራ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ማፍራት መቻላቸውን ይናገራሉ።

የጀመሩትን ስራ በጥምር ግብርና የማስፋትና የሚያገኙትን ወተት በማቀነባበር ምርቱን በተለያየ መልኩ ለገበያ የማቅረብ ራዕይን ሰንቀው በትጋት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በህገወጥ ስደት ካጋጠማቸው ችግር ተነስተው በተግባር ያዩትን ለሌሎች በማስተማር የስደትን አስከፊነት ለአካባቢያቸው ወጣቶች እያስገነዘቡ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ወጣቶች የስደትን አማራጭ ከመመልከታቸው በፊት የአካባቢያቸውን ፀጋ እንዲቃኙና ራዕይ ሰንቀው ራሳቸውን ለማሻሻል እንዲሰሩም መክረዋል።  

መለወጥ በውጪ ሀገር ብቻ ያለ የሚመስላቸው የቤተሰብ ኃላፊዎችም ልጆቻቸው በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ በማመን ሊያግዟቸው እንደሚገባም አቶ ገራድ አስገንዝበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትልና የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለምይርጋ ወልደስላሴ፤ በክልሉ በርካታ ወጣቶች ያልተጨበጠ ተስፋ ሰንቀው ለህገወጥ ስደትና ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡


 

በሀገር ሰርቶ ለመለወጥ የሚያስችል አቅም በግብርናው ዘርፍ መኖሩን ጠቅሰው በዘርፉ የተሰማሩ ከስደት ተመላሾች በአካባቢያቸው ሰርተው ለስኬት እየበቁ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከራሳቸው አልፈው ለበርካታ ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ላይ የሚገኙና የእነዚህን አካላት ተሞክሮ በመውሰድ በሀገር ሰርቶ ለመለወጥ መትጋት ይገባል ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም