ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ ይጠናቀቃል 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 23/2018 (ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት መርሐግብር በመጨረሻ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። 

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባምንጭ ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። ስድስት ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ አራት ግቦችን አስተናግዷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ12 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል። አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ግቦች ደግሞ ተቆጥረውበታል።

አርባምንጭ ከተማ በአራት ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር አዲስ አዳጊዎቹ ነጌሌ አርሲ እና ሸገር ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ነጌሌ አርሲ በሊጉ ካከናወናቸው ሰባት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ አምስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በዘጠኝ ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል። 

ሸገር ከተማ በበኩሉ ከስድስት ጨዋታዎች መካከል ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። አራት ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ በተመሳሳይ አራት ግቦችን አስተናግዷል። 

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሸገር ከተማ በስምንት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት መቻል ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

መቻል በሊጉ ባካሄዳቸው ሰባት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 11 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ12 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

በሊጉ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ያሸነፈው ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስምንት ግቦችን አስተናግዷል። 

ድሬዳዋ ከተማ በ10 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም