ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ሶስተኛ አላፊ ሀገር ለመሆን ዛሬ ከኬንያ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 23/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ከኬንያ አቻው ጋር የደረጃ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።

በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን  በግማሽ ፍጻሜው በዩጋንዳ 3 ለ 0 መሸነፉን ተከትሎ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ የመጀመሪያ እድሉን ሳይጠቀም ቀርቷል።

ቡድኑ ዛሬ ከኬንያ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ካሸነፈ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ያረጋግጣል።

ተጋጣሚዋ ኬንያ በግማሽ ፍጻሜው በታንዛንያ 3 ለ 1 መሸነፏ የሚታወስ ነው።


 

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በውድድሩ በምድብ አንድ የመጨረሻ ጨዋታ ተገናኝተው ኢትዮጵያ በዳዊት ካሰው ግብ 1 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ1997 ቦትስዋና ባዘጋጀችው ውድድር ላይ ነበር። 

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከኬንያ ጋር ለሶስተኛ ደረጃ እንዲሁም ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ከሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ አስቀድሞ ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን ማከናወኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። 

የማጣሪያው የፍጻሜ ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ላይ በታንዛንያ እና ዩጋንዳ መካከል ይደረጋል።

ሁለቱ ሀገራት ለፍጻሜ ማለፋቸውን ተከትሎ እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ ለሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ሀገራት በማጣሪያው በምድብ ሁለት የነበሩ ሲሆን እርስ በእርስ ባደረጉት ጨዋታ ታንዛንያ ዩጋንዳን 2 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ የፍጻሜውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራል። 


 

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከሕዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የሴካፋ ማጣሪያ ዛሬ ይጠናቀቃል።

በውድድሩ ላይ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ የሚወጡ ሀገራት የሴካፋ ዞንን ወክለው እ.አ.አ በ2026 በሞሮኮ አስተናጋጅነት በሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ላይ እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መረጃ ያመለክታል። 

በሞሮኮ አስተናጋጅነነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ራሷን ሞሮኮ ጨምሮ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም