ቀጥታ፡

በጤናው ዘርፍ የመንግስትን ጥረት በማገዝ ረገድ የማህበራዊ ተቋማት ሚና የላቀ ነው

ሀዋሳ ፤ ሕዳር 22/2018(ኢዜአ)፦ በጤናው ዘርፍ የመንግስትን ጥረት በማገዝ ረገድ የማህበራዊ ተቋማት ትብብርና ተሳትፎ ሚናው የላቀ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር  ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ ዋራ ቀበሌ በኢትዮጵያ ሃዋርያት ቤተክርስትያን ከ25 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የጤና ጣቢያን ርዕሰ መስተዳድሩ እና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) መርቀው ስራ አስጀምረዋል። 


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ በጤናው ዘርፍ መከላከልና ማከመን መሰረት በማድረግ መንግስት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከገጠር እስከ ከተማ የጤና ተደራሽነትን የማስፋትና የዜጎችን ጤና በመጠበቅ ረገድም ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

የጤና ተቋማትን በብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲሁም በቁሳቁስ የማሟላትና የማደራጀት ስራም እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። 

በመሆኑም በጤናው ዘርፍ የመንግስትን ጥረት በማገዝ ረገድ የማህበራዊ ተቋማት ትብብርና ተሳትፎ ሚናው የላቀ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል ።


 

በዋራ ቀበሌ የተገነባው ጤና ጣቢያ ለአካባቢው ህብረተሰብ የተሟላ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ጤና ጣቢያውን የተረከበ ሲሆን የላቦራቶሪ፣ ኤክስሬይ፣ አልትራ ሳውንድና ሌሎችም አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ በተሟላ ግብአትና የሰው ሃይል ተደራጅቶ ስራ ጀምሯል።


 

በኢትዮጵያ ሃዋርያት ቤተክርስትያን የተከናወነው ተግባር ለሌሎችም ተምሳሌት በመሆኑ ርእሰ መስተዳድሩ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም