ቀጥታ፡

ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ 

አዲስ አበባ፤ ሕዳር 22/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት መርሐግብር ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1 ለ 0 አሸንፏል። 

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ብርሃኑ በቀለ በአራተኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።

በውድድር ዓመቱ ስድስተኛ ድሉን ያስመዘገበው ሲዳማ ቡና በ19 ነጥብ የሊጉን መሪነት አጠናክሯል። 

በሊጉ ሁለተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስምንት ነጥብ ከነበረበት 12 ደረጃ ወደ 14ኛ ዝቅ ብሏል። 

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ሌላኛው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 ረቷል።


 

አቡበከር አዳሙ በ11ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በሊጉ ተከታታይ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ቡና በ10 ነጥብ ደረጃውን ከ15ኛ ወደ 10ኛ አሻሽሏል።

በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና በሰባት ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ዛሬ አስቀድሞ በተደረገ ጨዋታ ምድረገነት ሽሬ ሃዋሳ ከተማን 1 ለ 0 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም