ዲጂታል ግብርና፤ የአፍሪካ ግብርና አዲስ ምዕራፍ - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ግብርና፤ የአፍሪካ ግብርና አዲስ ምዕራፍ
ዲጂታል ግብርና በጥቅሉ ሲተረጎም የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ለግብርና ስራዎች መጠቀም ማለት ነው። ቴክኖሎጂዎቹ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት፣ በአቅርቦት የእሴት ሰንሰለት ላይ መጠናከር፣ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የአየር ንብረት ለውጥ አይገበገሬነት ስራዎችን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አላቸው።
የዓለም የዲጂታል ግብርና ገበያ እ.አ.አ በ2022 ከ10 እስከ 12 ቢሊዮን መድረሱን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። እ.አ.አ በ2028 የገበያ መጠኑ ከ23 እስከ 25 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ትንበያ ተቀምጧል።
የዲጂታል ግብርና በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና እስያ ፓሲፊክ በፍጥነት እያደገ ሲሆን በአፍሪካና ላቲን አሜሪካ ጅምር ላይ ነው ማለት ይቻላል። ሰሜን አሜሪካ 40 በመቶ እና አውሮፓ 25 በመቶ የዓለም የዲጂታል ግብርና ገበያ ድርሻን ይይዛሉ።
አርሶ አደሮች ለዲጂታል ግብርና የሚያስፈልጋቸውን ቴክኖሎጂዎችን አለማግኘት፣ የዳታ ደህንነት እና የግል መረጃ ጥበቃ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትና ባህላዊ ልማዶችን ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተሳሰር ዓለም አቀፍ የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው።
አፍሪካ ከአምስት እስከ ሰባት በመቶ(ከ500 እስከ 800 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር) የሚገመት ነው።
በአፍሪካ የግብርና ቴክኖሎጂ ያለው ኢንቨስትመንት በፍጥነት እያደገ ይገኛል። ዘርፉ ከ400 ሚሊየን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ፈሶበታል። በሞባይል የማማከር አገልግሎት፣ የገበያ ትስስር ማዕቀፎችና ለአርሶ አደሮች የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የቴክኖሎጂዎቹ የተደራሽነትና አላምዶ የመጠቀም ውስንነት፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ እክሎች እንዲሁ አካታችነት የአፍሪካ ፈተናዎች ናቸው። በአፍሪካ አብዛኛው ግብርና በአነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች ላይ የተመሰረተ ሲሆን ግብርና ለአፍሪካውያን ኑሮ እና የምግብ ዋስትና ወሳኝ የሚባል ነው።
በዚህ ረገድም የዲጂታል ግብርና ለግብርና ምርታማነት ማደግ፣ የአቅርቦት እጥረትን በመቅረፍና የልማት ግቦች በማሳካት ረገድ የበኩሉን ሚና ይጫወታል። ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በጥር ወር 2017 ዓ.ም የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ይፋ አድርጋለች።
በወቅቱ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከግብርና ሚኒስቴር እና የጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን ፍኖተ ካርታውን በጋራ ይፋ አድርገዋል። ማዕቀፉ ከዚህ ቀደም የነበሩ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና ማማከር አገልግሎቶች በአንድ ጥላ ስር ያስቀመጠ ነው።
ፍኖተ ካርታው የግብርና እሴት ሰንሰለቱን በሙሉ ዲጂታላይዝ የማድረግ አላማ አለው። የማማከርና የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ የገበያ መረጃ፣ ዲጂታል ክህሎት፣ ሜካናይዜሽን፣ የዳታ መረጃ አሰባሰብና ዲጂታል መሰረተ ልማት የፍኖተ ካርታው አበይት ትኩረቶች ናቸው።
መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን የዲጂታል ግብርናን ለማስፋት እየሰራ ነው። የአፍሪካ ህብረት ያዘጋጀው የመጀመሪያው የዲጂታል ግብርና ጉባኤ በአዲስ አበባ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
“ኢኖቬሽን እና የዲጂታል መፍትሄዎችን ለግብርና ዘርፍ በመጠቀም የአፍሪካን መጻኢ ጊዜ ብሩህ ማድረግ” የጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኅብረቱ ዲጂታላይዜሽንን የልማት አጀንዳው አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የግብርናው ዘርፍም በዚህ የዲጂታላይዜሽን አህጉራዊ ስትራቴጂ ውስጥ ትኩረት እንደተሰጠው አንስተዋል።
ኮሚሽኑ አባል ሀገራት ለዲጂታል ግብርና የመረጃ አጠቃቀምና አስተዳደር አመቺ ፖሊሲዎችን እንዲያዘጋጁ እና እንዲተገብሩ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት። ለአርሶ አደሮች፣ ለግብርና ባለሙያዎችና ለወጣቶች በዲጂታል ክህሎቶች ዙሪያ ሥልጠና እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።
በአፍሪካ ዲጂታል ግብርናን እውን ለማድረግ የአባል ሀገራት መንግስታት፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች እና የምርምር ተቋማት በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ አካባቢ ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ በበኩላቸው የአፍሪካን የግብርና ሥርዓት ለመለወጥ እና የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዲጂታል ግብርናን መተግበር የግድ ነው ብለዋል።
ዲጂታል ግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የምርት ብክነትን ለመቀነስ፣ የፋይናንስና የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲሁም የመቋቋም አቅምን ለመገንባት ቁልፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ወጣቶች የአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለኢኖቬሽንና ለዲጂታል ግብርና ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ዲጂታል ግብርናን እንደ ቁልፍ ስልት መውሰዷንና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዘርፉን ለማዘመን የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ በመድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን በስማርት ስልኮች አማካይነት ተደራሽ ማድረግ፣ ትክክለኛ የግብርና መረጃዎችን በአንድ ቋት መያዝና ማዘመን ላይ እየተሰራ መሆኑንና የግብርና ግብዓትን ተደራሽ ማድረግ፣ ከማሳ እስከ ገበያ ባለው ሂደት ውስጥ ያሉ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ለማጎልበት ዲጂታላይዜሽን ላይ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።
የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት፣ የግብርና ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን፣ የገበያ ተደራሽነት፣ የእሴት ሰንሰለትን ማጠናከር፣ የግብርና ምርታማነትን ከአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም መገንባት ጋር ያስተሳሰረ አካሄድን መከተል፣ የግብርና ፖሊሲዎችና የህግ ማዕቀፎች ትግበራ የኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች የሚመክሩባቸው አጀንዳዎች ናቸው።
ኮንፍረንሱ የእውቀት ሽግግር እና ፖሊሲ ተኮር ውይይቶች የሚደረግበት ሲሆን ስኬታማ የሀገራት የግብርና ኢኒሼቲቮች ለተሳታፊዎች ይቀርቡበታል።
በአፍሪካ የዲጂታል ግብርና መፍትሄዎችን ተደራሽነት የሚደግፉ ስትራቴጂዎች የመለየት እና አጋርነቶችን ማጠናከር ከሁነቱ የሚጠበቅ አበይት ውጤት መሆኑን ኢዜአ ከአፍሪካ ህብረት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢንተርኔት ተደራሽነት በሚፈለገው መጠን አለማደግ ፣ የዲጂታል ክህሎት ማነስ፣ የመሰረ ልማት ግንባታ እና የፖሊሲ ማዕቀፍ የዘርፉ ፈተናዎች ሲሆኑ ለአፍሪካ የዲጂታል ግብርና ትሩፋቶች ከፈተናዎቹ ይገዝፋሉ። ዲጂታል ግብርና ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት፣ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ኢኮኖመሚ ልማት አንቀሳቃሽ ሞተር የመሆን አቅም አለው።