በክልሉ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል
ወልቂጤ፤ ሕዳር 22/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) ተናገሩ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት የተዘጋጀ ኤግዚቢሽን እና ባዛር በወልቂጤ ከተማ ተከፍቷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ኤግዚቢሽንና ባዛሩን በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በዓሉን የምናከብረው የህዝቦችን አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ እህትማማችነት እና አብሮነትን በማፅናት ነው ብለዋል።
ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በክልሉ በዞኖችና በልዩ ወረዳዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱንም ጠቁመዋል።
እንደ ሃገር በክልሉ ሆሳዕና ከተማ ''ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ''በሚል መሪ ሀሳብ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በዓሉ ሀገራዊና ክልላዊ መግባባትን ለማጠናከር በህዝቦች መካከል ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማጎልበት የሚያግዙ የአብሮነት እሴቶችን የምናጠናክርበት ነው ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ በዓሉ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህላዊ እሴቶች አጉልቶ ለማሳየትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
ዞኑ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረው በፍቅር አብረው የሚኖሩበት እንደመሆኑ መጠን በከተማው ባዛርና ኤግዚቢሽን የጋራ እሴቶችን ለማሳየት እንደተዘጋጀም አስረድተዋል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
በኤግዚቢሽኑና ባዛሩ ላይ ከ200 በላይ የተለያዩ ምርቶች መቅረባቸው የተጠቆመ ሲሆን ከዛሬ ህዳር 22/2018 ዓ.ም እስከ ህዳር 27 /2018 ዓ.ም እንደሚቆይም ተመልክቷል።