ቀጥታ፡

በዓሉ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ገጽታ ግንባታ የላቀ አስተዋጾ አበርክቷል - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

ቡሌ ሆራ፤ ሕዳር 22/2018 (ኢዜአ)፡- የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል መከበር ሕብረ ብሔራዊ  አንድነትን በማጠናከር  ለሀገር ገጽታ ግንባታ የላቀ አስተዋጾ አበርክቷል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች  ቀን በዓል በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።


 

በበዓሉ አከባበር ላይ የተገኙት  የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ በዓሉ ኢትዮጵያውያን በጋራ ለመኖር የተስማሙበትና በየዓመቱ ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በአደባባይ የሚያንጽባርቁበት ነው።

ይህም ጠንካራ የፌዴራል ስርዓት እንዲኖር በማድረግ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን እያጠናከረ ለሀገር ገጽታ ግንባታ የላቀ አስተዋጾ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በዓሉ የእርስ በእርስ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ በየደረጃው ተከብሮ ሕዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና  ከተማ  በሀገር ደረጃ  እንደሚከበር አንስተዋል።


 

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን በበኩላቸው፤  በዓሉ በክልሉ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ትስስር በሚያጠናክር መልኩ ሲከበር ቆይቶ ዛሬ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዓሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባሕልና እሴቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ሕብረ ብሔራዊ አንድነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ቃላቸውን የሚያድሱበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ በዓሉ ታላቁ የኢትዮጵያ  ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ ሌሎች በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተጀመሩበት ወቅት መከበሩ ለሀገራዊ ልማት በጋራ በመቆም ዳግም ሕብረት የሚጠናከርበት ነው ብለዋል።


 

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዱላ ህርባዬ፣ በዞኑ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ያሉትን ፀጋዎች ወደ ልማት በመለወጥ የሕዝቡን  ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል ብለዋል።

በተለይ ቡናን ጨምሮ ሌሎች የቅባት እህሎች እንዲሁም በቁም እንስሳት ምርታማነት ውጤታማ ያደረጉ ተግባራት በዞኑ መከናወናቸውን  አንስተዋል።

በዓሉ በክልል ደረጃ በዞኑ መከበሩ የአካባቢውን ጸጋ ከማስተዋወቅ ባለፈ የተጀመሩ ልማቶችን ለማጠናከር ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም