የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ - ኢዜአ አማርኛ
የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል -ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ
ጋምቤላ፤ ህዳር 22/2018 (ኢዜአ)፦ የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ''ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በጋምቤላ ክልል ደረጃ በአኝዋሃ ዞን ዲማ ወረዳ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በክብረ በዓሉ ላይ እንዳሉት ህገ መንግስቱ ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያጎናፀፈውን መብት በመጠቀም የክልሉን ህዝብ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በዓሉን ስናከብርም የህዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት የሚሸረሽሩ እንቅስቃሴዎችን በመታገልና የህዝቦችን አንድነትና አብሮነትን በማፅናት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
በክልሉ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የተያዘውን የብልጽግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር የክልሉን ህዝብ ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች እንደሚጠናከሩም አብራርተዋል።
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችም ክልሉ ለጀመራቸው የዘላቂ ሰላምና የልማት ስራዎች መሳካት ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሯ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ ወይዘሮ መሠረት ማቲዎስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በዓሉ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኙበት ዕለት በመሆኑ ለክልሉ ህዝብ ልዩ ትርጉም አለው።
ጋምቤላ የክልሉ ህዝቦች ተቻችለውና ተከባብረው በፍቅር አብረው የሚኖሩበት አካባቢ እንደመሆኑ መጠን ይህንን የጋራ እሴቶች ጠብቆ ለትውልዱ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል ብለዋል።
በክልል ደረጃ ህገ መንግስቱ የፀደቀበትን ዕለት በዚህ መልኩ በድምቀት ማክበራችን የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት አጉልቶ ያሳያል ብለዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወይዘሮ አጁሉ ቶማስ በሰጡት አስተያየት በዓሉን የክልሉ ብሄሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በጋራ ማክበራችን አብሮነታችንና አንድነታችንን ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።
በዓሉ አንዱ የሌላውን ማንነት፣ ወግና እሴት እንድናውቅ እድል የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ለክልሉ ሰላምና ልማት መሳካት አበርክቶው የጎላ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ቱት ኒውት ናቸው።
ትናንት በሲምፖዚየም የተከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጋምቤላ ክልል ደረጃ በአኝዋሃ ዞን ዲማ ወረዳ እለቱን በሚያደምቁ መርሃ ግብሮች ተከብሮ ውሏል።