የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 22/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከመርሃ ግብሮቹ መካከል ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች አምስቱን ሲያሸንፍ ሽንፈት ያስተናገደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 11 ግቦችን ሲያስቆጥር አራት ግቦችን አስተናግዷል።
ሲዳማ ቡና በ16 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዟል።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ስምንት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ በተመሳሳይ ስምንት ግቦች ተቆጥረውበታል። ንግድ ባንክ በስምንት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። በአንጻሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ከቀናው ወደ አሸናፊነት መንገድ ይመለሳል።
በሌላኛው መርሃ ግብር ምድረገነት ሽሬ ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ምድረገነት ሽሬ በውድድር ዓመቱ ባካሄዳቸው ሰባት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በዘጠኝ ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል አራቱን በድል ሲወጣ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። በሰባቱ ጨዋታዎች ላይ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ጎሎች ገብተውበታል።
ሃዋሳ ከተማ በ13 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ያሸነፈው ኢትዮጵያ ቡና አራት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። በጨዋተያዎቹ ላይ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ግቦችን አስተናግዷል።
ቡናማዎቹ በሰባት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ እስከ ማሸነፍ የቻለው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሽንፈት ሲገጥመው በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። አምስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ ከተጋጣሚው እኩል ሰባት ነጥብ በመሰብሰብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 16ኛ ደረጃን ይዟል።