መደመራዊ የዝላይ የሽግግር ሂደት ሦስት ቁልፍ ነገሮችን ይይዛል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መደመራዊ የዝላይ የሽግግር ሂደት ሦስት ቁልፍ ነገሮችን ይይዛል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 21/2018 (ኢዜአ)፡- መደመራዊ የዝላይ የሽግግር ሂደት ወደ ውጤት መቀየር፣ ወደ ሌላ መሻገር እና ወደ ፊት መስፈንጠር የተሰኙ ቁልፍ ጉዳዮችን እንደሚይዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በመደመር መንግሥት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል ርዕስ ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ሰጥተዋል።
በዚሁ ወቅትም፤ መደመራዊ የዝላይ መንገድ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች እንዳሉት ጠቅሰው፤ አንደኛው ከቀዳሚው ጋር ያለ ልዩነትን በፍጥነት ማጥበብ ሲሆን ሁለተኛው እመርታዊ እድገት ማምጣት መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት መደመራዊ የዝላይ መንገድ ሌሎች የረገጡትን ሁሉ መርገጥ ተገቢ እንዳልሆነ፤ ውጤት ዐይተን ከዚያ መማር እንችላለን ብሎ እንደሚያነሳ ጠቁመዋል።
ጊዜ ወሳጅነትንና የአርፋጅነት ፈተናን ማሸነፊያ መሆን አለበት፤ ከሌሎች ውድቀትና ስኬት መማር፣ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ መማር ያስፈልጋል ብሎ እንደሚያምንም አመላክተዋል።
ነገር ግን እያንዳንዱን ዱካ መከተል ውጤታማ አያደርግም ብሎ ያነሳል ብለዋል።
በአጠቃላይ መደመራዊ የዝላይ የሽግግር ሂደት ሦስት ቁልፍ ነገሮችን እንደሚይዝ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ እነሱም ወደ ውጤት መቀየር፣ ወደ ሌላ መሻገር እና ወደ ፊት መስፈንጠር መሆናቸውን አብራርተዋል።
ይህ ማለትም ነባር ዐቅሞችን ወደ ውጤት መቀየር፣ አዳዲስ ዘርፎች መፍጠር ወደዚያ መሻገር፣ በዘርፎች ውስጥም የሚፈጠር ሽግሽግን መከወን፣ አዳዲስ የመልማት ዐቅሞች ማውጣት፣ አዳዲስ የገበያ ዕድሎች መፍጠርን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
አክለውም፤ ያለንን ዐቅም ማዘመን፣ ወደ ዓለም መስፈንጠር፣ መዋቅራዊ ሽግግግር ማረጋገጥ፣ ዕውቀትን እንደ ምርት መጠቀም ብሎም ከፈተና ውስጥ ሊፈለቀቅ የሚችል ዕድል ካለ ችግርን ወደ ዕድል መቀየር ይጠበቃል ሲሉ አስረድተዋል።