ቀጥታ፡

የተሳሳተ መንገድ በመከተል የበደልነውን ህዝብ ለመካስ የመንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል - የቀድሞ ታጣቂዎች 

ጎንደር፤ ህዳር 21/2018(ኢዜአ)፦ የተሳሳተ መንገድ በመከተል የበደልነውን ህዝብ ለመካስ ይቅርታ በመጠየቅ የመንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ሲሉ በአማራ ክልል እጃቸውን የሰጡ የቀድሞ ታጣቂዎች ተናገሩ። 

የመንግስትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 15 የቀድሞ ታጣቂዎች በጎንደር ከተማ የቡድን መሳሪያ ጨምሮ የነፍስ ወከፍ ትጥቃቸውን ለመንግስት በማስረከብ በሰላም ገብተዋል፡፡ 


 

ታጣቂዎቹ በዚሁ ጊዜ በሰጡት አስተያየት የተሳሳተ መንገድ በመከተል መሳሪያ ይዘን ጫካ በመግባት  የበደልነውን ህዝብ ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል። 


 

በጥፋታችን በመፀፀት ህዝብን በስራ ለመካስና የሰላም አምባሳደር ለመሆን የመንግስትን የሠላም ጥሪ ተቀብለን መጥተናል ሲሉም ገልጸዋል። 


 

ከታጣቂዎቹ መካከል አስናቀ ሽጉጥ፣ በክልሉ በትጥቅ እንቅስቃሴ በሽፍትነትና ዘረፋ መሠማራታችን ለህዝብ የመታገል አላማ የሌለው መሆኑን በተግባር አይተናል ብሏል። 

በመሆኑም በተሳሳተ መንገድ በህዝብ ላይ ላደረስነው በደል ተፀፅተናል፤ በልማት ለመካስም የሰላምን መንገድ መርጠን መጥተናል ብሏል። 

ሌሎችም ይህንኑ እድል በመጠቀም ውለው ሳያድሩ ማህበረሰባቸውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አስተላልፏል። 


 

ሌላኛው የሰላምን መንገድ መርጦ እጁን የሰጠ የቀድሞ ታጣቂ መብራቱ ወርቁ፣ በሰለጠነ ዘመን ጦር መሣሪያን አማራጭ ማድረግ ከጥፋት በስተቀር መፍትሄ እንደማይሆን በመረዳት ሰላምን መርጠን መጥተናል ብሏል። 

በመሆኑም ሌሎች በጫካ የሚገኙ ወንድሞች ትጥቅ ፈትተው ሰላምን መርጠው መምጣት እንደሚኖርባቸውም መክሯል። 


 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዠ ኮማንደር አንተነህ ቴዎድሮስ በበኩላቸው፣ የሰላምን አማራጭ የተከተሉ 15 የቀድሞ ታጣቂዎች የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያቸውን በማስረከብ ማህበረሰቡን ለመቀላቀል መምጣታቸውን ገልፀዋል። 

ከዚህ በፊት የመጡ ታጣቂዎችን መልሶ በማቋቋም ሰላማዊ ህይወት እንዲመሩ መደረጉን አስታውሰው ለእነዚህም ተመሳሳይ ስራ ይሰራል ብለዋል። 

አሁንም ቢሆን በጥፋት ውስጥ ተሰልፈው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት የተሰጠውን የሰላም እድል ለመጠቀም እንዲመጡ ጠይቀዋል። 

በሁሉም አካባቢዎች ሰላምን በማፅናት የልማት ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የፀጥታ ሃይሉ ከህዝቡ ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም