የመደመር መንግሥት መዳረሻ ሁለንተናዊ ብልጽግና ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት መዳረሻ ሁለንተናዊ ብልጽግና ነው -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 21/2018 (ኢዜአ)፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት መዳረሻ ሁለንተናዊ ብልጽግና መሆኑን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በመደመር መንግሥት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል ርዕስ ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ሰጥተዋል።
በዚሁ ወቅትም የመደመር መንግሥት መዳረሻ ሁለንተናዊ ብልጽግና መሆኑን ገልጸው፤ ሁለንተናዊ ማለትም ግብረገብነትን በማያበላሽ መልኩ ትጋትና ዘመኑን የዋጀ ብቃት ደምሮ መያዝ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ሁለንተናዊ ብልጽግና ማለት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሁሉን ነገር በውስጡ ያሟላ መሆኑንም አብራርተዋል።
ይህ ማለትም የበለጸገ ግን ያልሰለጠነ፤ የሰለጠነ ግን ያልበለጸገ ሰው እንዳይኖር መትጋት ማለት መሆኑን ነው ያስረዱት።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሀገራዊ ብልጽግና አእማዶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ እነሱም ኢኮኖሚ (ከሁሉም ለሁሉም በሁሉም)፣ ፖለቲካ (አካታችና አሳታፊ) እና ማኅበራዊ (ትውልዳዊ ልማት) የሚሉት መሆናቸውን አብራርተዋል።
የመደመር ትውልድ ቁልፍ ጥያቄዎችም ኢትዮጵያ ምን ትምሰል?፣ መንግሥት ምን ይምሰል? እና ትውልድ ምን ይምሰል? የሚሉት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በመደመር ትውልድ የኢትዮጵያ መልክና ቅርጽ፤ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያለባት፣ የወንድማማችነት እሴትን ያጸናች፣ የሲቪክ ባህል የጎለበተባት እና ቀጣናዊ ትስስሮችን ያጠናከረች ናት ሲሉ ገልጸዋል።
ማስተካከል፣ማስፋፋት እና ማበርከት የመደመር ትውልድ መርሆዎች መሆናቸውንም አመላክተዋል።
እንዲሁም በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ዲጂታል ዓርበኝነት፣ የትምህርት ተሃድሶ፣ የባህል ኢንዱስትሪ የትውልድ ግንባታ ስትራቴጂዎች ናቸው ብለዋል።