ቀጥታ፡

በከማሺ ዞን አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ነው

አሶሳ፤ህዳር 21/2018(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሺ ዞን አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን የሀገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የከማሺ ዞን አስተዳደር ዞን በበኩሉ ዞኑ የነበረበትን የፀጥታ ችግር በመፍታት ሙሉ በሙሉ ወደ ሠላም እንዲመለስ በመደረጉ የዞኑ ነዋሪዎች ሠላማዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

የከማሺ ዞን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ ሶስት ዞኖች አንዱ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የፀጥታ ችግር ይስተዋልባቸው ከነበሩ አካባቢዎች አንዱ ነው።

በአሁኑ ወቅት ግን የፀጥታ ኃይሉ ከሀገር ሽማግሌዎችና አጠቃላይ ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ ባከናወኗቸው በርካታ ተግባራት ዞኑ ሰላሙ ተመልሶ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት አዙሯል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች የአካባቢው ሠላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ የሀገር ሽማግሌዎች ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።

ከዞኑ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታደሰ ሻምበል የፀጥታ ችግሩን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የፀጥታ አካላት እና የሀገር ሽማግሌዎች የማግባባት ስራ በመስራትና ውይይትን እንደ አማራጭ መፍትሔ በማድረግ የዞኑ ሠላም እንዲመለስ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ይህም ዞኑ ወደ ልማት እንዲመለስ እና ህብረተሰቡም በግብርና፣በማዕድን ልማትና በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የከማሺ ዞን የተለያዩ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመከባበርና በአብሮነት የሚኖሩበት ነው ብለዋል።

የሠላምን አስፈላጊነት እና የፀጥታ ችግር የሚያደርሰውን ጉዳት ሁሉም የዞኑ ነዋሪ ተረድቷል የምትለው ደግሞ ሌላዋ የዞኑ ነዋሪ መስቀሌ ዱጉማ ነች።

በአሁኑ ወቅት በዞኑ ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ መኖሩን በመግለጽ።

የከማሺ ዞን የሀገር ሽማግሌ አቶ አሻግሬ ቄሌ በበኩላቸው፤ የፀጥታ ችግሩን በውይይት ለመፍታት የተደረገው ጥረት ውጤታማ ነበር ብለዋል።

በተደረገው ባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርዓት በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች በሠላም ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉና በዞኑ አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን መደረጉን ገልጸዋል።

የከማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ ፃፊዮ ዞኑ የነበረበትን የፀጥታ ችግር በመፍታት ሙሉ በሙሉ ወደ ሠላም እንዲመለስ በመደረጉ የዞኑ ነዋሪዎች ሠላማዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም