ቀጥታ፡

የበዓሉ መከበር ሀገራዊ መግባባቱ እንዲዳብርና በብዝሃነት ውስጥ ያለው አንድነት እንዲጠናከር የላቀ ሚናን ይጫወታል

ጋምቤላ፤ ህዳር 21 /2018 (ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል መከበር ሀገራዊ መግባባቱ እንዲዳብርና በብዝሃነት ውስጥ ያለው አንድነት እንዲጠናከር የላቀ ሚናን ይጫወታል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ መሠረት ማቲዎስ ገለፁ። 

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ''ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሃሳብ  በክልል ደረጃ በአኝዋሃ ዞን በዲማ ወረዳ በፓናል ውይይትና ሌሎች መርሃ ግብሮች እየተከበረ ነው። 


 

ዛሬ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ አፈ-ጉባኤዋ እንዳሉት የበዓሉ መከበር ሀገራዊ መግባባቱ እንዲዳብርና በብዝሃነት ውስጥ ያለው አንድነት እንዲጠናከር የላቀ ሚናን ይጫወታል። 

በክልሉ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብሮነታቸውን በማጠናከር በጋራ እንደሚኖሩ ገልጸው የበዓሉ መከበርም ይህን መስተጋብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል። 

የበዓሉ በየዓመቱ መከበር አንዱ የሌላውን ባህል፣ እሴትና ወግ እንዲረዳ የሚያደርግ በመሆኑ ዕለቱ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠዉ ነው ብለዋል። 

የፓናል ውይይቱ ዋና ዓላማም ትክክለኛ በሆነው የፌደራሊዝም እሳቤ ዙሪያ ሀገራዊ መግባባትን ለማዳበር ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አፈ-ጉባኤዋ አስረድተዋል። 


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በመድረኩ ላይ እንዳሉት የክልሉ ህዝብ ህገ-መንግስቱ ያጎናፀፈውን መብት ተጠቅሞ በኢኮኖሚያዊ ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ያለውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያጎለበተ መጥቷል። 

በዓሉ በጋራ መከበሩ በጠንካራ ሀገራዊ መግባባት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ የተዛባ ትርክትን ለማስተካከልና ብዝሃነትን በአግባቡ ለማስተናገድ እንደሚያስችል ገልፀዋል።   

በፓናል ውይይቱ ላይ ''ዲሞክራሲና የፌዴራል ስርዓት በኢትዮጵያ፣ ተስፋዎችና ተግዳሮቶቹ'' በሚል ርዕስ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። 

በነገዉ ዕለትም 20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በክልል ደረጃ በአኝዋሃ ዞን በዲማ ወረዳ አዘጋጅነት በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት ይከበራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም