የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያ ትክክለኛ መልክ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያ ትክክለኛ መልክ ማሳያ ነው
ቡሌ ሆራ ፤ህዳር 21/2018 (ኢዜአ)፡- የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያ ትክክለኛ መልክ ማሳያ መሆኑ ተመላከተ።
20 ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በቡሌ ሆራ ከተማ በፓናል ውይይትና በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) በውይይት መድረኩ ላይ እንደተናገሩት የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ባህላዊ እሴቶች እንዲተዋወቁ ድርሻው የጎላ ነው፡፡
የውስጣዊ ጥንካሬ ምንጭ የሆነውን የብሔሮች፤ ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴት በማጎልበት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያን ትክክለኛ መልክ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።
የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ አቶ ሌኒን ቁጦ በበኩላቸው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ግንኙነት የሚጠናከርበት እለት መሆኑን ገልጸዋል።
የብሔሮች ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴት የሰላም፣ የአገራዊ አንድነትና በጋራ የመኖር መሠረት መሆኑን አንስተው ለዚህም የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ጥሩ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የገዳ ሥርዓት የሰላም ምንጭ መሆኑን የገለፁት የጉጂ አባ ገዳ ጃርሶ ዱጎ የብሔሮች፤ ብሔረሰቦችን ቀን ስናከብር ጠቃሚ እሴቶችን ከማጉላት ባለፈ የእርስ በእርስ ትስስራችንን ለማጠናከር በመስራት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ይህም ሰላማችንን ከማጽናት ባለፈ አገራዊ ተሰሚነታችንንም ያሳድጋል ሲሉም አክለዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን፣ አባ ገዳዎችና አደ ሲንቄዎች እንዲሁም የቡሌ ሆራ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
ቀኑ ከፓናል ውይይት በተጨማሪ በባህላዊ አልባሳት አውደ ርዕይና ባዛር እንዲሁም በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል፡፡