የኢትዮጵያ ኩራት በሆነው የአየር ኃይል 90ኛ ዓመት የጎዳና ላይ ሩጫ በመሳተፋችን ክብር ይሰማናል- የውድድሩ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኩራት በሆነው የአየር ኃይል 90ኛ ዓመት የጎዳና ላይ ሩጫ በመሳተፋችን ክብር ይሰማናል- የውድድሩ ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፤ህዳር 21/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የአየር ክልል በትጋት በመጠበቅ የኢትዮጵያዊያን ኩራት በሆነው የአየር ኃይል 90ኛ ዓመት የጎዳና ላይ ሩጫ በመሳተፋችን ክብር ይሰማናል ሲሉ የውድድሩ ተሳታፊዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በማስመልከት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
የጎዳና ላይ ሩጫው ‟ለአየር ኃይል ዕድገት በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ” በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው።
በመርሀ ግብሩ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ፣የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣የሠራዊት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ኢዜአ በውድድሩ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎችም የኢትዮጵያ ኩራት በሆነው አየር ኃይል የተመሰረተበትን 90ኛ ዓመት የጎዳና ላይ ሩጫ በመሳተፋቸው ክብር እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
ከተሳታፊዎቹ መካከል ዮናስ ደበላ አየር ኃይል የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላምና ሉዓላዊነትዊ ደህንነት የጀርባ አጥንት ተቋም መሆኑን ገልጿል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ መሰለ ታዬ በበኩላቸው አየር ኃይል ባለፉት 90 ዓመታት ትልልቅ ታሪክ እና ድል ያስመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያንም ከውጭ እና ከውስጥ ጠላት የታደገ በልፋት እና ትጋት ዛሬ ላይ የደረሰ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
አየር ኃይል እንደ ሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው ተቋም መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ ፍሬዘር አሰግድ ናት።
ለመላው የሠራዊቱ አባላትም የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፋለች።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ገመዳ ፊዳሞ አየር ኃይል የኢትዮጵያን የአየር ክልል በማስጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድም የበለጸገች ኢትዮጵያን የሚያስተላልፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ጌታ ያውቃል አሸናፊ በበኩሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነ ተቋም መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለልማት እና ሀገር እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጸችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጭ መብሩክ አህመድ ናት።