በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ ወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ማበርከት አለበት -ትዴፓ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ ወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ማበርከት አለበት -ትዴፓ
አዲስ አበባ፤ህዳር 21/2018(ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ ወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ማበርከት እንዳለበት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/ ትዴፓ / ገለጸ።
የቀድሞ ህወሃት በትግራይ የሚያካሂዳቸው እንቅስቃሴዎች በህዝብ ላይ እንደመቀለድ የሚወሰድ መሆኑንም ገልጸዋል።
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/ ትዴፓ / በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ሙሉብርሃን ሃይሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የክልሉ ሕዝብ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ወጣቱ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በተለይም ክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ወጣቱ በመጪው ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ጠቁመው፤ለዚህም በፖለቲካ ሂደቱ ወጣቱ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያስችሉት ተግባራትን ፓርቲያቸው እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ሁሉም የሚሳተፍበት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ፓርቲ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ የማድረግ ስራ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተዋል።
ከዚህ ውስጥም ከተለያዩ አደረጃጀቶች፣ ልሂቃን እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ከሲቪክ ማሕበራት ጋር በቅንጅት የመስራት ጅማሮ መኖሩንም አስታውቀዋል።
ፓርቲው ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመጪው ምርጫ ለመወዳደር እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ከምንም በላይ የሚፈልገው ሰላም፣ልማትና ዲሞክራሲ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ለማሳካት የጋራ ትግል እንደሚያስፈልግ ነው ዋና ፀሐፊው አቶ ሙሉብርሃን የገለጹት።
ህዝቡ ያለ ስጋት ስለ ልማት እንዲያስብ የሁሉም ዜጋ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የቀድሞ ህወሃት በትግራይ ክልል መጪው ምርጫ እንዳይሣካ ለማድረግ የሚያከናውናቸው ተግባራት በህዝብ ላይ እንደመቀለድ የሚወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከህወሓት ተፈጥሯዊ ባሕርይ አኳያ ሰላማዊ ትግልን የሚሸሽና የማይፈልግ ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ የቡድኑ አባላት በሃሳብ የበላይነት የማያምኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይልቁንም በክልሉ ብጥብጥና ሁከት በመፍጠር ምርጫ ለማወክ፣በግርግር ስልጣን ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም አንስተዋል።
ማንኛውም ወገን ለሕዝብ ሰላምና እድገት የሚያስብ ከሆነ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ለምርጫ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበትም ነው የጠቀሱት።