ቀጥታ፡

የማያግባቡ ጉዳዮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት እሴቶችን ልናጠናክር ይገባል - ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም

ጋምቤላ፤ ህዳር 21/2018 (ኢዜአ)፡- የማያግባቡ ጉዳዮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት እሴቶችን ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም ገለጹ።

የሴቶችን፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞችን ሚናና አስተዋጽኦ ለውጤታማ ሀገራዊ የምክክር መድረክ በሚል መሪ ሃሳብ በጋምቤላ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።


 

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት በህዝቦች መካከል የማያግባቡ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በውይይትና በምክክር የመፍታቱ ሂደት አትራፊና ዘላቂ ሰላምን የሚገነባ እሴት ነው።

ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ሂደቶች ጎጂና ዘላቂ ሰላምን የማያመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም እንደ ሀገር ያጋጠሙ አለመግባባቶችና ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እያካሄደ ላለው ሂደት መቃናት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በሀገር ደረጃ የሚነሱ ሃሳቦች ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሂደት ግብዓት መሆናቸውን ገልጸው፤ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ዘላቂ ሰላም ግንባታ ሀሳቡን ሳይሰስት ማንሳት ይገባል ብለዋል።

በተለይም የማያግባቡ ጉዳዮችን በውይይትና በምክክር የመፍታት ወርቃማ ባህላዊ እሴቶችን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ሁሉም በየአካባቢው ጠንክሮ ሊስራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በውይይቱ ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ ለሌሎች በማከፈል ረገድም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

በጋምቤላ ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም