ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር የባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውናና የትውልድ ዋነኛ ጥያቄ ነው

መቀሌ፤ህዳር 21/2018 ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር የባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውናና የትውልድ ዋነኛ ጥያቄ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ተመላከተ።

ኢትዮጵያ የባህር በር ህጋዊ፣ ታሪካዊና መልክዓ ምድራዊ ባለቤት የነበረች ቢሆንም ግልፅና አሳማኝ ባልሆነ መልኩ እንድታጣው ተደርጓል።

በዚህም ምክንያት ለብዙ ችግር በመዳረግ ብዙ ዋጋ እየከፈለች ከ30 ዓመታት በላይ በመዝለቋ አሁን ላይ ጉዳዩ የትውልድ ጥያቄ እና ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ሆኗል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ካህሳይ ሙሉ፣ ኢትዮጵያ ያለ ባህር በር ተቆልፎባት መቀጠል አትችልም፣ ከህልውናዋ ጋር ተያይዞ የባህር በር ባለቤት መሆኗ ግድ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በየትኛውም መመዘኛ ህጋዊ መሰረትና ተቀባይነት ያለው ስለመሆኑ አንስተው፥ ምላሽ ማግኘት ያለበት ተገቢ ጥያቄ ስለመሆኑ አንስተዋል።

በአፍሪካ በህዝብ ብዛት በ2ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ መድኃኒትን ጨምሮ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን ለማስገባት ያለባህር በር አዳጋች መሆኑ የማይቀር ነው ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር የባለቤትነት ጥያቄ የሀገር ህልውናና የትውልድ ዋነኛ ጥያቄ በመሆኑ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የባህር በር ጉዳይ ከኢኮኖሚና ማህበራዊ ጠቀሜታውም ባሻገር የደህንነትና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ተገቢና ቀና ምላሽ ማግኘት ያለበት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም በጉዳዩ ላይ የተያዘውን የዲፕሎማሲ ጥረት አድንቀው፥ የእያንዳንዳችን ጥረትና እገዛ ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዓለም አቀፍ አጀንዳ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የተያዘው የዲፕሎማሲ ጥረት ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተው፥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም