የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2018(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያን ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን ይበልጥ በማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን በማፅናት ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።
በአዲስ አበባ ከተማ የ20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ከተማ አቀፍ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ የክልሎች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን እሴቶቻቸውን፣ ባህላቸውንና ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት የኢትዮጵያ ቀን ነው ብለዋል።
ቀኑ ኢትዮጵያዊያን ብዝኃነታቸውን የሚያሳዩበት ህብረ-ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበትና ለዘላቂ ሰላም፣ ለፈጣን ልማትና ኢኮኖሚ እድገት የሚወያዩበትና ቃል የሚገቡበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የአገሪቷ ህዝቦች በጋራ ሆነው በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበት እና የአገሪቷን አንድነት ለማጽናት በድጋሚ ቃል የሚገቡበት መሆኑን ገልጸዋል።
ህዝቦች የበለጠ የሚተዋወቁበት፣ አንድነትና ትስስር የበለጠ ጎልቶ የሚታይበት ቀን መሆኑን ጠቁመዋል።
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አንድነትና ወንድማማችነት የሚጠናከርበት በዓል መሆኑን ጠቁመዋል።
የዘንድሮው በዓል ለሀገራዊ መግባባት ተግዳሮት የሆኑ ችግሮችን በውይይትና በምክክር በመፍታት ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማፅናት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በጀመርንበት ወቅት የሚከበር ነው ብለዋል።
ውይይትና ምክክር አማራጭ ሃሳቦችን በማቅረብ ልዩነትን ለማጥበብና የወል ሃሳብ በማፍለቅ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።
ሀገርን ወደ ብልፅግና የማሸጋገር ጉዞን ለማሳካት፣ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ማጠናከር በውይይትና በምክክር ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነት ካላቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን ጠቅሰው፤ ባለፉት መንግስታት ብዝሃነትን በአግባቡ ከማስተናገድና ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ከመጠቀም አኳያ ጉድለቶች እንደነበሩ አንስተዋል።
ብዝኃነትን ለሀገራዊ አንድነትና ለብሔራዊ መግባባት ማዋል ይገባል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ለዚህም መላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል።
የዘንድሮ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በሚያጎላ መልኩ በብዝሃነት ደምቆ እንደሚከበር ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው፤ ቀኑ ብዝሃ ማንነት የሚንጸባረቅበት ነው ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የህዝቦች ትስስርን በማጠናከር አብሮነት የሚጎላበት ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ ይከበራል።