ለሀገራዊ የምክክሩ ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ የምክክሩ ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኮሚሽኑ
ጋምቤላ፤ ህዳር 20/2018(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ የምክክሩ ስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም ገለጹ።
''የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር'' በሚል መሪ ሀሳብ በጋምቤላ ከተማ ዛሬ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እየተካሄደ ነው።
ኮሚሽነሩ በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት በምክክር ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ሴቶችና አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ለችግሮች መፍትሄ ለማበጀት በሚደረገው ጥረት የማይተካ ድርሻ እንዳላቸው አንስተዋል።
ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ሴቶች፣ ወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ያላቸውን አቅም በመጠቀም የተጀመረውን ሀገራዊ የምክክር ማሳካት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ምክክር በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ የታለመውን የሰላም ግንባታ ለማሳካት በትኩረት እንድሚሰራም አስረድተዋል።
የዛሬው መድረክም ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምምክር መድረኩ የተሳትፎና የአጋርነት ሚናቸውን ለማጠናከር በማለም መሆኑንም ጠቅስዋል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በነፃነትና በእውነት ላይ የተመሰረተ ጠቃሚ ሃሳቦችን በማዋጣት በኩል የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።
በጋምቤላ ከተማ በተዘጋጀው የሁለት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።