የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መሰረት ያለው ነው
ደሴ፤ ሕዳር 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ እና ሕጋዊ መሰረት ያለው መሆኑን በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ገለጹ።
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው የሉአላዊነትና የትውልዱ የሕልውና ጉዳይ እንዲሁም ሕጋዊና ታሪካዊ መሰረት ያለው እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በባሕር በር የባለቤትነት ጥያቄ ዙሪያ ኢዜአ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ጋሻው መሐመድ(ዶ/ር) እና የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኘነት መምሕር እንድሪስ ሁሴንን አነጋግሯል።
ምሁራኑ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በሸፍጥ ያጣችውን የባሕር በር ባለቤትነት ማስመለስ ሕጋዊ መሰረት ያለው የሕልውና ጉዳይ ነው።
አሁን የተመዘገበውን ፈጣን እድገት ለማስቀጠልና ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን ይበልጥ ለማጉላት የባሕር በር ባለቤትነት ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።
ይህም እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ማስተናገድ የሚያስችል እድገትን ለማስቀጠልና ከቀጣናው ሀገራት ጋር በጋራ ለመልማት አጋዥ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም የባሕር በር ጥያቄው አግባብነት ታሪካዊና ህጋዊ መሰረት ያለው እንዲሁም ዜጎች ለተግባራዊነቱ ርብርብ እያደረጉበት ያለ እውነታ መሆኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ባሕር በር ፍላጎት የትውልዱ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ በመተባበር የባሕር በር ባለቤት የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።
የሀገሪቱን ታሪካዊና ሕጋዊ ጉዳዮች በማስተሳሰር የባሕር በር ባለቤትነትን ለማሳካት የተሄደበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁንም ዲፕሎማሲንና ኢኮኖሚያዊ አጋርነትን መሰረት ተደርጎ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ሁሉም ሚናውን መወጣት እንዳለበት ያመለከቱት ምሁራኑ፤ የሀገሪቱ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።