የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ አድርጓል
ጎንደር ፤ ሕዳር 20/2018(ኢዜአ)፡ - በጎንደር ከተማ በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ የእግረኛ መንገዶች ከትራፊክ አደጋ ስጋት ነፃ ሆነን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንድንችል ምቹ በመሆኑ ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ አካል ጉዳተኞች ተናገሩ።
በከተማው ከፒያሳ አዘዞ አውሮፕላን ማረፊያ የሚዘልቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ በአሁኑ ወቅት በፍጥነትና በጥራት እየተካሄደ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጓዴ ደመቀ፤ በከተማው የተገነባው የኮሪደር ልማት አካል ጉዳተኞች ምቹ ፅዱና አረንጓዴ በሆኑ አካባቢዎች እንዲዝናኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ነበሩ የመሠረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንደልነበር አስታውሰው፤ የኮሪደር ልማቱ ሰፊ የእግረኛ መንገድን ያካተተ በመሆኑ ከትራፊክ አደጋ ነፃ ሆነን መንቀሳቀስ እንድንችል በማመቻቸት ተጠቃሚ አድርጎናል ሲሉ ገልጸዋል።
በከተሞች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት የአካል ጉዳተኞችን ደህንነት ያስጠበቀና ሀገሪቱ አለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶችንና ድንጋጌዎችን ያስከበረች መሆኗን ይበልጥ ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ነባር መንገዶች አብዛኞቹ የእግረኛ መንገድ የተሟላላቸው ባለመሆናቸው በተለይ አካል ጉዳተኞች በተሽከርካሪ አደጋ ይደርስባቸው ነበር ያሉት ደግሞ አቶ ጸጋው ውቤ ናቸው፡፡
አሁን ላይ በኮሪደር ልማቱ የተገነቡት የእግረኛ መንገዶች፤ የመዝናኛና የማረፊያ ስፍራዎች አካል ጉዳተኞች ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ ለመንቀሳቀስና ለመዝናናት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ዳዊት ጥጋቤ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ከመፍጠር በዘለለ አካል ጉዳተኞችም እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
የከተማው በነባር መንገዶች በስፋት ይስተዋል የነበረው ያልተደፈኑ የፍሳሽ ቦዮችና የግንባታ ቁሳቁሶች ለአደጋ ያጋልጣቸው የነበረው ችግር ሁሉ በኮሪደር ልማቱ መፈታቱን አንስተዋል።
የከተማው ነዋሪ አቶ መስፍን አበራ፤ የኮሪደር ልማቱ ለከተማችን መልካም እድሎችን ይዞ የመጣ፤ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል የፈጠረና ለአዲስ የስራ ባሕል ሕዝቡን ያነሳሳ ነው ብለዋል።፡
የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማት ምቹ የመኖሪያና የስራ አካባቢን በመፍጠር ከተማውን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ በኩል የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የገለጹት የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ናቸው።
ከፒያሳንና የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስቱን አካባቢ ያካተተው የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ ባለፈው ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱን አስታውሰዋል።
12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውና ከፒያሳ አፄ ቴዎድሮስ ሀውልት እስከ አዘዞ አየር ማረፊያ የሚዘልቀው ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ በፍጥነትና በጥራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን ጨምሮ የአረንጓዴ መናፈሻ ፖርኮችን እንዲሁም ስማርት መጸዳጃና ዘመናዊ የመንገድ ዳር የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ያካተተ ነው።