ቀጥታ፡

የበለፀገችና ህብረብሄራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው - ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ አንድነቷ የጸና የበለፀገችና ህብረብሄራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ጋር በመተባበር ወጣቶች ለሰላም ግንባታና ለማህበራዊ ትስስር መጠናከር በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ "አዲስ ፎረም 2025" እየተካሄደ ይገኛል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ወጣቶች ለሰላም፣ አንድነት፣ አብሮነት፣ ለሀገር ብልፅግና ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡

መንግሥት አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ወጣቶች ለሀገር ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አንድነቷ የፀና፣ የበለፀገችና ህብረብሄራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት ወጣቶች ያላቸውን አቅም በመጠቀም ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

"የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሰላምና ደህንነት ሀገራዊ የድርጊት መርሃግብር" መጠናቀቁን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ለገቢራዊነቱ የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶች እና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው፤ ወጣቶች ግንባር ቀደም የሰላም ዘብ የመሆን ሀገራዊ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ለዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት የወጣቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ ወጣቶች ልማት ላይ በስፋት እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለአመራርነት ለማብቃት በክህሎት ልማት ላይ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወጣት ኢንጂነር ጫላ አሰፋ፤ ሰላም እያንዳንዳችን የምንገነባው የጋራ ህንፃ መሆኑን ገልጿል።

ሰላም የሁሉ ነገር መነሻና መሰረት፤ ለልማትና አንድነት ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፤ ማህበሩ ወጣቶች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መሀንዲስ፣ የለውጥ መሪ እንዲሆኑም ተናግሯል።

የፎረሙ ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው ወጣቶች በሀገር ግንባታና ሰላም የላቀ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸው የሚናቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም