ቀጥታ፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ሂደት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይገባል -ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሀገራዊና አህጉራዊ ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ሂደት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ75ኛ ዓመት አልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል አካል የሆነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጋሮች መርሃ ግብር ተካሂዷል።


 

በመርኃ ግብሩ የትምህርት ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው ቻንስለር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር)፣ ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት አብረው የተጓዙ አጋሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በዚህም "ለዘላቂ ልማት እና ለአፍሪካ መጻኢ ዕጣ ፈንታ የከፍተኛ ትምህርት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ለሀገራት ሁለንተናዊ እድገት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ወሳኝ ነው።

የተማረ የሰው ኃይልን በማፍራት እንዲሁም በጥናትና ምርምር ስራዎች ዘላቂ ልማትን የማረጋገጥ ሂደት ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።


 

የደቡብ ደቡብ ትብብር ምክትል ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው፤ ዘላቂ ልማት የሚለካው በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ብቻ ሳይሆን በእውቀትና በእሴት መጎልበት እንዲሁም በማህበረሰብ ለውጥ ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዘላቂ ልማት መረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላቸው ሚና ቁልፍ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመድረኩ የፓናል ውይይት ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት እመቤት መለሰ (ዶ/ር) ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዘላቂ ልማት ላይ ስርዓተ ትምህርት ቀርፀው መስራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ የድህረ ምረቃ ጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም፥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማህበረሰብ ተኮር ምርምር እና ፈጠራ ላይ የማተኮር ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በጥናት ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ አወጣጥ ላይ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ወሳኝ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የባዮ እና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካሳሁን ተስፋዬ ናቸው።

በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች የሀገራዊ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ለማዘጋጀት የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችን ማፍለቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም