ኢትዮጵያ ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የፍትህ ተቋማትን መፍጠር የሚያስችል ሀገራዊ ሪፎርም አድርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የፍትህ ተቋማትን መፍጠር የሚያስችል ሀገራዊ ሪፎርም አድርጋለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የፍትህ ተቋማትን መፍጠር የሚያስችል ሀገራዊ ሪፎርም ማድረጓን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ገለጹ።
የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ከፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ፈዴራል ጠበቆች ማህበር ጋር በመተባበር 30ኛ ዓመት የምሥረታና ዓመታዊ ጉባኤውን በአፍሪካ ሕብረት ማካሄድ ጀምሯል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በለውጡ ዓመታት ከሀገር አልፎ ቀጣናውን የሚያስተሳስሩ የዲሞክራሲ ተቋማትን መፍጠር የሚያስችል ጥረት እያደረገች ነው።
በዚህም ባለፉት ዓመታት ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የፍትህ ተቋማትን መፍጠር የሚያስችል ሀገራዊ ሪፎርም ማድረጓን ተናግረዋል።
በፍትህ ዘርፉ የተደረገው ሪፎርም የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ህጋዊና ገለልተኛ ተቋም ሆኖ እንዲፈጠር አስችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ከአምስቱ የፍትህ ዘርፍ መሰረቶች አንዱ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።
ይሄውም ኢትዮጵያ በሀገራዊ ሪፎርሙ የፍትህ ተቋማትን ለማጠናከር የወሰደችውን ወሳኝ እርምጃ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የህግ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበርና የሌሎች የቀጣናው ሀገራት የፍትሕ ተቋማት ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ አምባሳደር ሞሐመድ ኤል አሚን ሱፍ የምስራቅ አፍሪካ የህግ ማህበረሰብ የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063ን ግብ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል።
በአፍሪካ ሀገራት ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓት በሚያደርጉት ሽግግር የፖለቲካ መረጋጋትን ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት አባል ሀገራት መልካም አስተዳደር ዲሞክራሲና ፍትሕን ለማስፈን የሚሰሩበት ጊዜ አሁን ነው ያሉት ሀላፊው፤ ሕብረቱ የተለያዩ የዲሞክራሲ ተቋማትን በማቋቋም ለፍትህ ስርዓት መስፈን አባል ሀገራትን እየደገፈ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ የዲሞክራሲ አስተዳደርና የምርጫ ቻርተር፣ የአፍሪካ ሰላምና ደህንነት አርክቴክቸር ግጭትን በመከላከል ሰላምን ማስፈን የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የያዛቸውን አጀንዳዎች ከግብ ለማድረስ የፍትሕ ተቋማትና የህግ ባለሙያዎች ለመልካም አስተዳደር መስፈንና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
የሕብረቱ አባል ሀገራት የጋራ እሴቶቻቸውን በማጎልበት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፤ የምስራቅ አፍሪካ የህግ ማህበረሰብ ወጣት የህግ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ለህግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር መስፈን ሚናውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ ፕሬዝዳንት ረመዳን አቡበከር፤ ተቋሙ በቀጣናው ፍትሕን በማረጋገጥ የህግ የበላይነት የማስፈን ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
የሕግ የበላይነትና ዲሞክራሲ በራሱ የሚቀጥል ሳይሆን በየጊዜው ልምምድን የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት፤ የዲሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ካልተቻለ አለመረጋጋት ይፈጠራል ብለዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ በሽዎች የሚቆጠሩ ወጣት የህግ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ለአፍሪካ ሕብረት መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ግብ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣናው በተከፋፈለ መንገድ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እንደማይቻል ገልጸው፤ የምሥራቅ አፍሪካ የሕግ ማህበረሰብ በሀገራት መካከል የህግ ስርዓት ትብብር እንዲፈጠር ሚናውን ይወጣል ብለዋል፡፡
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር ኢትዮጵያ በፍትህ ተቋማትን ለማጠናከር የጀመረችውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ጌታቸው የምስራቅ አፍሪካ የህግ በማህበረሰብ የቀጣናው ስትራቴጂካዊ አጋር ሆኖ እንደሚቀጠል ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ዜጎችን የፍትሕ እጦት ለመፍታት፣ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ሚናውን ይወጣል ብለዋል፡፡
ከምስራቅ አፍሪካ የህግ ማህበረሰብ ጋር በትብብር በመስራት የቀጣናውን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳለጥ አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር ለፍትህ ዘርፉ ዕድገት ገንቢ ሚና እንዳለው በማንሳት፤ ተቋሙን ለማጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል፡፡