ትልልቅ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ የተግባቦት ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል-ከፍተኛ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ትልልቅ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ የተግባቦት ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል-ከፍተኛ አመራሮች
አዲስ አበባ፤ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ትልልቅ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት የኅብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያጎለብቱ የተግባቦት ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።
በብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀቶች የኢኮኖሚ ክላስተር አዘጋጅነት የፖለቲካ ትንተና፣ማህበራዊ ሚዲያና ሁኔታ ትንተና ላይ በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የአሰልጣኞች ስልጠና መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በሥልጠና መርሃ ግብሩ ላይ በፌደራል ተቋማት አደረጃጀቶች የኢኮኖሚ ክላስተር የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊዎችና የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትርና በብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል ተቋማት አደረጃጀቶች የኢኮኖሚ ክላስተር ሰብሳቢ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት፤ አመራሩ በሪፎርም ሥራዎች በመታገዝ ትልልቅ የልማት ግቦችን ለማሳካት እየተጋ ነው።
እነዚህ የልማት ግቦች የሚሳኩት በሕዝቡና በመንግሥት መካከል መሰናሰል ሲፈጠር ነው ያሉት አቶ መላኩ፥ ህብረተሰቡን በልማት አጀንዳዎች ላይ በተሻለ መልኩ የሚያሳተፉ የተግባቦት ሥራዎችን በትኩረት ማከናወን ይገባል ብለዋል።
አመራሩ እየተለዋወጠ ባለው የዓለም ሁኔታ ያሉ ዕድሎችን ለመጠቀም ወቅቱን የዋጀ እውቀት በመጨበጥ ህዝቡን በውጤታማነት የማሳተፍ ሥራን ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ሥልጠናው በመረጃ ላይ በመመስረት ከሕዝቡ ጋር ይበልጥ ተናቦ ለመስራት ምቹ አውድ የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ በበኩላቸው፥ በመደመር መንግሥት እይታ ፈጣንና ፈጠራ የታከለበት አገራዊ አድገት ለማረጋገጥ ግብ ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ግቡን በውጤታማነት ለማጠናቀቅ በየጊዜው የፖለቲካ ትንተና ላይ የተመሰረቱ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመው፥ ለዚህም አመራሩ ራሱን ዝግጁ ማድረግ እንዳለበት አመልክተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ መሀመድ እድሪስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኢኮኖሚ አመራሩ አካታች ኢኮኖሚ ግንባታ፣ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና መሰል ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ቀርጾ መሥራት ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፣ የከተሞች ፎረምን ጨምሮ ሕዝቡን በማሳተፍ በውጤታማነት እየተተገበሩ ያሉ አጀንዳዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ መሰል ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
አመራሩ ፖሊሲዎችን ወደ አጀንዳነት መቀየር ላይ በሰፊው ሊሰራበት የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የብልፅግና ስትራቴጂ ጉዳይ ዋና ዳይሬክተር ተተካ በቀለ በበኩላቸው፤ የድህረ እውነት ፈተናዎች የሆኑትን ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን መታገል ላይ አመራሩ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።