የሀረር የኮሪደር ልማት የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ከመጠበቅም ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ እንዲሆን አስችሎታል - ኢዜአ አማርኛ
የሀረር የኮሪደር ልማት የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ከመጠበቅም ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ እንዲሆን አስችሎታል
ሐረር፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ):- የሀረር የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ከመጠበቅም ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ እንዲሆን አስችሎታል ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ተናገሩ።
በቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፤ የተመራው የአምባሳደሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ልዑካን ቡድን በሀረሪ ክልል የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን ጎብኝቷል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ፤ የመርሃ ግብሩ ዓላማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እና የቱሪዝም ሚኒስቴር በመተባበር የቱሪዝም መዳረሻዎችንና ሃብቶችን የመጎብኘት ነው ብለዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት የባሌ ብሔራዊ ፓርክን እንዲሁም ቀደም ሲል ሌሎች የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን መጎብኘታቸውን አስታውሰው በዛሬው እለት ደግሞ በጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ ሌሎችም የመስህብ ስፍራዎች መጎብኘታቸውን ገልጸዋል።
በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ ለዘማናት ተጠብቆ የቆየ ሃብት መሆኑን አንስተው አሁን ላይ ይበልጥ ለጎብኝዎች ምቹ እና ማራኪ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።
በሀረር ከተማ የተከናወኑ የኮሪደርና ሌሎች የከተማ ልማት ስራዎች የጀጎልን ዓለም አቀፍ ቅርስ ከመጠበቅም ባለፈ ለጎብኚው ውብ፣ ምቹና ማራኪ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።
በመሆኑም ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶችና እና የአለም አቀፍ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ቅርሱን የጎበኙት መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ከ40 በላይ እንግዶች መሳተፋቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ የኢትዮጵያን ቅርሶችና የቱሪዝም ሃብቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።