አፍሪካ የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ ልማትና ዕድገቷን ለማረጋገጥ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ ልማትና ዕድገቷን ለማረጋገጥ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ አፍሪካ የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ ልማትና ዕድገቷን ለማረጋገጥ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ገለጹ።
ፕሬዝደንቱ አፍሪካ በታሪኳ ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፤ ተቋማትን ማጠናከር፣ ዲሞክራሲ፣ መረጋጋትና ዕድገት ወሳኝ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
4ኛው የአፍሪካ ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤቶች እና መሰል ተቋማት አለም አቀፍ ሲምፖዝየም "ህገ መንግስታዊነት እና ሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ቴዎድሮስ ምህረት በዚሁ ወቅት፤ አፍሪካ ለሕገ-መንግሥታዊነት እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ ማስቀጠል ይኖርባታል ብለዋል፡፡
አፍሪካ ቁልፍ የሕዝብ አገልግሎቶችን መስጠት የሚችሉ የተረጋጋ ተቋማትን በመገንባት እና ተቋማዊ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎች መሥራት እንደሚጠበቅባትም ገልጸዋል፡፡
የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥና የሰብአዊ መብቶችን ለማጠናከር የአስተዳደር ሁኔታን ከማሻሻል ባሻገር የአህጉሪቱን ልማት ማፋጠን መሠረታዊ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የዚምባብዌ ጠቅላይ ዳኛ እና የአፍሪካ የሕገ-መንግሥት የዳኝነት አካላት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሉክ ማላባ በበኩላቸው አህጉሪቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገባች መሆኗን ጠቁመው፤ አፍሪካውያን በራሳቸው መተማመንና የለውጥ አጀንዳቸውን መምራት እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአፍሪካ ህብረትን መሠረታዊ መርሆች ማስጠበቅ እና አፍሪካውያን የራሳቸውን የለውጥ አጀንዳዎች መምራት እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አፍሪካ በወሳኝ ምእራፍ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ አምባሳደር መሐመድ ኤል-አሚኒ ናቸው።
ተቋማትን ማጠናከር፣ዲሞክራሲ እንዲሁም ዕድገት ወሳኝ የሆነበት ወቅት መሆኑን ጠቁመዋል።
ጠንካራና ነጻ የዳኝነት አካላት ሕጎች በፍትሐዊ መንገድ መተግበራቸውን፣ መብቶች መጠበቃቸውንና ሥልጣን በኃላፊነት መያዙን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።