ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እየተደረጉ ነው

ድሬዳዋ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ገለጹ።

20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በአስተዳደሩ የተዘጋጀው የንግድ ባዛር ዛሬ በይፋ ተከፍቷል።


 

የንግድ ባዛሩን የከፈቱት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፈትህያ አደን፣ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እና ሌሎች አመራሮች ናቸው።

በእዚህ ወቅት የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ገበያውን በማረጋጋት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግም የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን ከማቋቋም ባለፈ ከአጎራባች ክልሎችና በከተማዋ ካሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዛሬው ዕለት 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ የተከፈተው የንግድ ባዛር የዚሁ ገበያን የማረጋጋት ሥራ አካል መሆኑንም አመልክተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጠሃ በበኩላቸው፤ ምርትን በበቂ ደረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት የምርት አቅርቦታቸውን እንዲያሳድጉ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቅናት በሚቆየው የንግድ ባዛር ላይ የንግድ ተቋማት እና ኢንተርፕራይዞች የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።

ኢንተርፕራይዞቹና ተቋማቱ ባዛሩ ሸማቹን ከነጋዴዎች በቀጥታ በማገናኘት የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ ለገበያ መረጋጋት ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም