ተማሪዎች ህብረ ብሔራዊ አብሮነትን እንዲላበሱ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ተማሪዎች ህብረ ብሔራዊ አብሮነትን እንዲላበሱ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ ህብረ ብሔራዊነት አብሮነትን እንዲላበሱ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ርዕሳነ መምህራን ገለጹ።
በየዓመቱ ህዳር 29 የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዜጎች የአካባቢያቸውን አለባበስ፣ አመጋገብ፣ ቋንቋ፣ ባህልና እሴት የሚያስተዋውቁበት ታላቅ ኩነት ነው።
ኢዜአ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በትውልዱ እንዲሰርጽ እና ህብረ ብሔራዊ አብሮነት እንዲጎለብት የትምህርት ተቋማት ሚናን በተመለከተ የትምህርት ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
የቂሊንጦ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ኢሳያስ ገብረሚካኤል፤ ኢትዮጵያ ብዝሃ ባህል ያላት በመሆኑ ይህንኑ ሀብት ለዓለም ለማስተዋወቅ ቀኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።
የትምህርት ዘርፉ ተዋናዮች ትውልዱ የኢትዮጵያን ህብረ ብሔራዊ ውበት በአግባቡ በመገንዘብ ሀገሩን በተገቢው ልክ እንዲያውቅ የማስቻል አደራ አለብን ብለዋል።
የአጋዚያን ቁጥር ሶስት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ገነት ፊጣ በበኩላቸው፤ ቀኑ ትውፊቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዚህም ሁላችንም የሌላውን ባህል የማክበር ልማዳችንን ማጠናከር አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
በተለይም ተማሪዎች የብሔር ብሔረሰቦችን ብዝሃ ባህል እና ማንነት በአግባቡ እንዲያውቁ ቀኑን መሰረት በማድረግ ግንዛቤአቸውን የማሳደግ ስራ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የኮከበ ፅባህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ደለለኝ አስማረ እንደሚሉት፤ ቀኑ ቀጣይነት ባለው መልኩ መከበሩ በህዝቦች መካከል ያለውን መልካም መስተጋብር የሚያጠናክር ነው።
በዚሀም ተማሪዎች የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ እንዲገነዘቡ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ተማሪዎች የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህል፣ ወግና እና እሴት በጭውውትና በክበባት አማካኝነት እንዲገነዘቡ እየሰሩ መሆኑን የድልበር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህር ተመስገን ቶሊና አስታውቀዋል።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ ይከበራል።