ቀጥታ፡

በተለያዩ አካባቢዎች እገታ እና ዘረፋ እየፈፀመ ባለው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ ነው

ባሕርዳር፤ ሕዳር 19/2018(ኢዜአ)፡- በተለያዩ አካባቢዎች እገታ እና ዘረፋ እየፈፀመ ባለው ፅንፈኛ ቡድን ላይ በሕዝቡና የጸጥታ ሃይሉ ትብብር የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢ ጠናን ወረዳ ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይችላል አድማሱ፤ በአካባቢው በፅንፈኛው ቡድን ላይ እርምጃ በመውሰድ ሰላምን በማፅናት ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ፅንፈኛ ቡድኑ በጃቢ ጠናን ወረዳና አካባቢው በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተሹለከለከ በነዋሪዎች ላይ እገታ፣ ዘረፋና ግድያ በመፈፀም ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ለማድረግ መሞከሩን አንስተዋል። 

ከዚህም በመነሳት በሕዝቡ ጥቆማና ትብብር እንዲሁም በጸጥታ ኃይሉ የተጠና አካሄድ በፅንፈኛው ቡድኑ ላይ ጠንካራ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

በዚህ  የሕግ ማስከበር ስራም ከአርሶ አደሩ፣ ከባለሃብቶችና፣ ከእርሻ ልማት የተዘረፈ ከ649 ኩንታል በላይ እሕል ተከማችቶ መገኘቱን ጠቅሰዋል። 

በሕግ ማስከበር ስራ በተለይም የሕዝቡ ጥቆማ፣ ትብብርና እገዛ የላቀ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይም የተጠናከረ የሕግ ማስከበር ስራ ይከናወናል ሲሉ አረጋግጠዋል።

በአማራ ክልል በዞን፣ በወረዳ እና ከተሞች የተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰሞኑን ተከታታይ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን፤በውይይቱም የፅንፈኛ ቡድኑ የጥፋት እንቅስቃሴ በስፋት የተነሳ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም