በስልጠናው የአካባቢ ጸጋዎችን ለይቶ ጥቅም ላይ በማዋል ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ግንዛቤ አግኝተናል - ኢዜአ አማርኛ
በስልጠናው የአካባቢ ጸጋዎችን ለይቶ ጥቅም ላይ በማዋል ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ግንዛቤ አግኝተናል
ሀዋሳ፤ህዳር 19/2018 (ኢዜአ)፡-የአካባቢ ጸጋዎችን ለይቶ ጥቅም ላይ በማዋል ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ግንዛቤ ማግኘታቸውን የሲዳማ ክልል ሰልጣኝ አመራሮች ተናገሩ።
በክልሉ “በመደመር መንግስት ዕይታ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ ለመካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሥልጠናው ተሳታፊዎች በስልጠናው የአካባቢ ጸጋዎችን ለይቶ በማልማት ጥቅም ላይ ማዋልና ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ከሰልጣኝ አመራሮች መካከል የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ኢያሱ ነጆ (ዶ/ር) እንደተናገሩት የተቀናጀ የግብርና ምርት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ግብአቶችን በስፋት ይጠቀማሉ።
በስልጠናው ግብርናውና ኢንዱስትሪው ተመጋግበው እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚቻልና በዚህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ግንዛቤ መጨበጣቸውን ገልጸዋል።
"በተለይ በአካባቢ ያሉና ያልታዩንን ጸጋዎች ጥቅም ላይ በማዋል ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ አቅም የፈጠረልን ነው" ያሉት ኢያሱ (ዶ/ር) ፣ በቀጣይ ያገኙትን አቅም ተጠቅመው ለዘርፉ ለስኬታማነት ጠንክረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መቅደስ ሁሪሶ በበኩላቸው እንዳሉት ከተማዋ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች ቢኖራትም ባላት ሀብት ልክ ፀጋዎቿን አልምቶ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም።
ከስልጠናው በእጅ ያሉ ሀብቶችን ተጠቅሞ የሀዋሳን የቱሪስት መዳረሻነት ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የሀዋሳ ሐይቅ እና ታቦር ተራራን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪዎች ሠላማዊነትና እንግዳ ተቀባይነት ከተማዋን በጎብኚዎችና ባለሀብቶች ተመራጭ እንዳደረጋትም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በቀጣይ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዘው የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር ገጽታዋን ይበልጥ ለማጉላትና ከዘርፉ የሚገኝ ጥቅምን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።
ሥልጠናው አመራሩ በየሴክተሩ ያለውን አቅም ለይቶ ለውጤታማነት በቅንጅት መስራት የሚችልበትን አቅም የገነባበት ነው ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደስታ ዳንቾ ናቸው፡፡
በተለይ የመንገድ መሠረተ ልማት ግብርናና ኢንዱስትሪው በተሳለጠ መልኩ እንዲመጋገቡ፣ የቱሪዝም ተደራሽነት እንዲሰፋና ሌሎች ልማቶች እንዲፋጠኑ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል።
በመሆኑም ይህን የዘርፉን አስተዋጾ ለማጠናከር በስልጥና ያገኙትን አቅም ተጠቅመው ለውጤታማነት ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡
ለክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በተገኙበት ትናንት ማምሻውን እንደተጠናቀቀ መዘገቡ የሚታወስ ነው።