የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ተጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በጋራ አከበሩ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ተጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በጋራ አከበሩ
ደብረ ብርሃን፤ ሕዳር 19/ 2018(ኢዜአ)፡- የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢ ነዋሪዎች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን የእህትማማችነትና የወንድማማችነት እሴትን በሚያጎለብት መልኩ በጋራ አከበሩ።
በዓሉን በጋራ ያከበሩት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራና በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ቅንቢቢት ወረዳዎች ተጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የቅንቢቢት ወረዳ አፈ-ጉባዔ አቶ አስታጥቄ ገመቹ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በጋራ መከበር የሁለቱን አጎራባች ወረዳዎች ነዋሪዎች ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል።
በዓሉን በጋራ ስናከብርም ለዘመናት የዘለቀውን የእህትማማችነትና የወንድማማችነት እሴት በማጎልበት በአካባቢያችን ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት ይበልጥ የሚያነሳሳ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአንጎለላና ጠራና ቅንቢቢት ወረዳዎች አጎራባች ነዋሪዎች በባሕልና በማሕበራዊ ግንኙነት የተሳሰሩ በመሆኑ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር በጋራ መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የአንጎለላና ጠራ ወረዳ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ገነት ይገዙ በበኩላቸው፤ በዓሉን በጋራ ስናከብር አንድነታችንን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ልማት መጎልበት ለመሰራት በመነሳሳት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የሁለቱ ተጎራባች ወረዳዎች ነዋሪዎች በባሕል፣ በጋብቻና በማሕበራዊ ግንኙነት ጠንካራ ትስስር እንዳላቸው ጠቁመው፤ ይህንን በማላቅ የተጀመሩ የልማትና የሰላም ስራዎች እንዲጠናከሩ በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ኮኮቤ ማንበግሮት በሰጡት አስተያየት፤ በዓሉን በጋራ ማክበራቸው የጋራ ባሕልና እሴቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የቅንቢቢት ወረዳ ነዋሪ አቶ ኩራባቸው ተክለስላሴ በበኩላቸው፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በጋራ ማክበሩ አብሮነትን መሰረት ያደረገ ልማት ላይ በማተኮር እንድንተጋ ያግዛል ሲሉ ገልጸዋል።
በሁለቱም ተጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ትስስራቸውን የበለጠ በማጎልበት ለጋራ እድገታቸው በቅንጅት እንደሚተጉ የበዓሉ ተሳታፊዎች አረጋግጠዋል።