አሰብ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት፤ ቀይ ባህር ደግሞ መውጫ መግቢያዋ ሆኖ ወደ ነባራዊ እውነታው ሊመለስ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አሰብ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት፤ ቀይ ባህር ደግሞ መውጫ መግቢያዋ ሆኖ ወደ ነባራዊ እውነታው ሊመለስ ይገባል
ሰመራ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ አሰብ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት፤ ቀይ ባህር ደግሞ መውጫ መግቢያዋ ሆኖ ወደ ነባራዊ እውነታው ሊመለስ ይገባል ሲሉ የአፋር የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ህጋዊ፣ ታሪካዊና መልከዓ ምድራዊ መብት የነበራት ቢሆንም ምክንያቱ እና ውሳኔ ሰጪው ባልታወቀበት ሁኔታ ከባለቤትነት እንድትርቅ ተደርጋ ለዓመታት ዘልቃለች።
በዚህ ምክንያት ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት የባህር በር ባለቤትነት የሀገር ህልውና እና የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ መጥቷል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በትውልዱ ዘንድ ጥያቄ ሆኖ ከሶስት አስርተ ዓመታት በላይ የዘለቀ ሲሆን አሁን ላይ የህልውና ጉዳይ ሆኖ በሰላማዊ መንገድ የማግኘት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፋር የሀገር ሽማግሌዎች አሰብ የኢትዮጵያ አካሏ፤ ቀይ ባህር ደግሞ መግቢያ መውጫ በሯ ሆኖ ለዘመናት ስለማገልገሉ በታሪክ የተዘመገበ እና ዓለም የሚያውቀው ሃቅ መሆኑን አንስተዋል።
የአፋር ክልል ህዝብ ደግሞ ቀይ ባህር አቅራቢያው እያለ የተቆለፈበትና ከባህሩ የተገለለ ሆኖ በፍጹም ሊኖር የማይገባ በመሆኑ መብቱ ሊከበርለት ግድ ይላል ሲሉ አንስተዋል።
ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ጅብሪል ዓሊ እና አቶ ኡስማን ኢብራሂም፤ ኢትዮጵያ በአቅራቢያዋ ከሚገኘው ቀይ ባህር ተነጥላ ፈፅሞ ልትቀጥል አይገባም ብለዋል።
በመሆኑም አሰብ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት፤ ቀይ ባህር ደግሞ መውጫ መግቢያዋ ሆኖ ወደ ነባራዊ እውነታው ሊመለስ ይገባል ነው ያሉት።
በየትኛውም መመዘኛ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከቀይ ባህር መነጠል አይገባም በማለት አፅንኦት ሰጥተው ለመብታችን መከበር ህጋዊና መሰረታዊ ጥያቄያችን ይቀጥላል ብለዋል የሀገር ሽማግሌዎቹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በጋራ ከመጠቀምም ባለፈ የህይወት እና የደህንነት ጉዳይ በመሆኑ የግድ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ኡስማን ተናግረዋል።
ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ መሐመድ ሰኢድ፤ የአሰብ እና የቀይ ባህር ጉዳይ ታሪካዊና ህጋዊ መብታችን ሆኖ ሳለ በዝምታ መኖራችን ሁላችንንም ያስቆጨ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ግን ትክክለኛ ምላሽ የሚሻ የሀገር ህልውና እና የትውልድ ጥያቄ በመሆኑ በአፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።