ገዢ ትርክትን በመገንባት አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ገዢ ትርክትን በመገንባት አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ይጠናከራሉ
ሚዛን አማን፣ ኅዳር 19/2018 (ኢዜአ)፡- ገዢ ትርክትን በመገንባት አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመላከተ።
"ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሀገራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ በዓል በሚዛን አማን ከተማ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን እንዳሉት ብዝሃነትን ማስተናገድና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥ ለሀገር ግንባታ ትልቅ አቅም ነው።
በዚህ ረገድ በክልሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ለልማት ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማበርከታቸውን አንስተዋል።
ይህን ተሞክሮ ለማስቀጠልም ነጠላ ትርክቶችን በማረም ገዢ ትርክትን በመገንባት አንድነትንና ወንድማማችነትን በማጎልበት ረገድ የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።
የክልሉን ፀጋ ወደ ሀብት ቀይሮ ብልጽግናን ለማረጋገጥም ገዢ ትርክትን መገንባት መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ በበኩላቸው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ባህልና ሌሎች እሴቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበትን እድል ማስፋቱን ተናግረዋል።
ሕገ መንግሥቱ ለብሔሮችና ብሔረሰቦች መብት መከበርና እኩልነት ያለው አበርክቶ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዳገዘም አመልክተዋል።
አንድነትን በብዝኃነት ውስጥ በመገንባት ለልማት የሚውልበትን አቅም እናጠናክራለን ያሉት ደግሞ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ጌታቸው ኬኒ ናቸው።
ልዩነቶችን አክብሮ ለሀገር ብልጽግና መተባበር ላይ ሁሉም አቅሙን እንዲያዋጣም አሳስበዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ሀብተማርያም ካዚንቴት እንዳሉት አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት የበዓሉ መከበር የራሱ ድርሻ አለው።
በተለይም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት ማክበራቸው ባህልና ቋንቋቸውን ለማሳደግና እርስ በርስ ለመተዋወቅ እንደሚያግዝም አክለዋል።
በተለያየ ባህል፣ ቋንቋና ማንነት ውስጥ ያለውን የአብሮነት ትስስር ለትውልድ ለማስተላለፍ መሰል ኩነቶች ጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ አቶ ፀጋዬ ኮርጅቴት ናቸው።