ለቀጣናዊ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ልህቀት እውቅና የሚሰጠው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት - ኢዜአ አማርኛ
ለቀጣናዊ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ልህቀት እውቅና የሚሰጠው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት
የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት የተጀመረው በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አማካኝነት ነው።
ሽልማቱ የኢጋድ የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ እና ተቋማዊ አቅምን የማጠናከር ጥረቶች አካል ነው።
በኢጋድ ቀጣና በጋዜጠኝነት የላቀ ስራ ላከናወኑ የሚዲያ ባለሙያዎች በሽልማቱ እውቅና ይሳጣቸዋል።
ሽልማቱ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ህትመት፣ ፎቶግራፍ፣ ዲጂታል ሚዲያ እና ሌሎችም ተጓዳኝ መድረኮችን የሚሸፍን ነው።
የሚዲያ ስራው በቀጣናው በተለይም የድርቅ አይበገሬነት፣ ሰላም፣ ደህንነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ልማት ያሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆን ይኖርበታል።
ዓመታዊው የኢጋድ ሽልማት የቀጣናዊ ተቋሙ አባል ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ በግላቸው የሚሰሩ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች እና የፎቶ ጋዜጠኞች ጨምሮ አጠቃላይ የሚዲያ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ነው።
በተጨማሪም የቀጣናውን ጉዳይ የሚሸፍኑ የውጭ ሀገራት ጋዜጠኞችም ይሳተፉበታል።
በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ስራቸውን በእንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ እና በኢጋድ አባል ሀገራት በሚገኙ ቋንቋዎች ያቀርባሉ።
ከተለያዩ ሙያዎች የተወጣጡ የውሳኔ ሰጪ ወይም ገምጋሚ ቡድን ተቋቁሙ ስራዎቹን በመመዘን አሸናፊዎችን ይለያል።
የመጀመሪያው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት የተካሄደው እ.አ.አ በ2023 በጅቡቲ ነበር።
“የድርቅ ተጽእኖዎችን መቋቋም የሚያስችል ትብብር መፍጠር” የሽልማቱ መሪ ሀሳብ ነው።
መሪ ሀሳቡ በድርቅ፣ አይበገሬ አቅም መገንባት፣ የውሃ አስተዳደር እና ቀጣናዊ ትብብር ያተኮረ ነው።
ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ህትመንት፣ ጦማር (ብሎግ) እና የፎቶ ጋዜጠኝነት የሽልማት ዘርፎቹ ናቸው።
በመጀመሪያው ሽልማት ላይ ከቀጣናው 105 ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን 14 ባለሙያዎች በዘርፎቹ ተመርጠው ተሸልመዋል።
የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት ተቋሙ ሚዲያን ለግንዛቤ መፍጠር እና ቀጣናዊ ትብብር እንደ መሳሪያ ለመጠቀም ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ በወቅቱ ገልጾ ነበር።
በድርቅ እና በምግብ ዋስትና ላይ ያሉ የጋራ ፈተናዎችን ለመፍታት የሚዲያ ሚና ወሳኝ እንደሆነም አመልክቷል።
ሁለተኛው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት የተካሄደው እ.አ.አ በ2024 በኬንያ ናይሮቢ ነው።
“የተስፋ ትርክቶች፤ የቀጣናውን መጻኢ ጊዜ ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ እና ሁሉን አቃፊ ማድረግ” የሽልማቱ መሪ ሀሳብ ነው።
ሽልማቱ በሰላም፣ ደህንነት፣ ሁሉን አሳታፊ የሆነ መጻኢ ጊዜን መፍጠር፣ ቀጣናዊ ትብብር እና መረጋጋት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ህትመት፣ ፎቶግራፍ፣ ዲጂታል ሚዲያ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የእድሜ ዘመን ተሻላሚ ከሽልማት ዘርፎቹ ውስጥ ናቸው።
ለ2024ቱ ሽልማት 318 የሚዲያ ባለሙያዎች ስራቸውን ያቀረቡ ሲሆን 18 የሚዲያ ባለሙያዎች በዘርፎቹ ሽልማት አግኝተዋል።
ሁለተኛው ሽልማት ከመጀመሪያው በዘርፎች እና በተሳታፊዎች ብዛት መሻሻል የታየበት ነበር። ይህም ሚዲያ በቀጣናዊ ሰላም፣ ደህንነት እና ቀጣናዊ ትስስር ላይ ያላቸውን ሚና የሚያሳይ ነው።
ሶስተኛው የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት ወደ አፍሪካ መዲና አዲስ አበባ መጥቷል። ሽልማቱ ነገ ህዳር 20 እና 21 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
የሽልማት ስነ ስርዓቱ “ ውጤታማ የአየር ንብረት ዘገባ ደህንነቱ ለተረጋገጠ፣ ጠንካራ እና የተረጋጋ ቀጣና” በሚል መሪ ሀሳብ የሚከናወን ነው።
ኢጋድ ቀጣናዊ ሁነቱን ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ነው።
ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያና የአፍሪካ ኢምፖርት እና ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪኤግዚም ባንክ) ለፕሮግራሙ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታውቋል።
የዚህ ዓመት ሽልማት በአፍሪካ ቀንድ ውጤታማ የአየር ንብረት ትርክትን ለቀረጹ ጋዜጠኞች እና የፊልም ባለሙያዎች እውቅና የሚሰጥ ነው።
የሁለት ቀን ሁነቱ የአየር ንብረት ጠንካራ ዘገባዎች እና ሀሳቦች የሚቀርቡበት እንዲሁም ቀጣናዊ ትብብር ጎልቶ የሚታይበት መሆኑን ኢጋድ ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
የ2025 የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት በ10 ዘርፎች የሚከናወን ነው።
የህትመት ጋዜጠኝነት፣ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት፣ የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት፣ ዲጂታል ሚዲያ፣ ፎቶግራፈር፣ ሀገር በቀል ዘገባ፣ የዓመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ/ የይዘት ቀራጭ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እና የእድሜ ዘመን ሽልማት የሽልማት ዘርፎቹ ናቸው።
400 የሚሆኑ የኢጋድ አባል ሀገራት ባለሙያዎች ስራዎቻቸውን ማስገባታቸውን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ 94 የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች መሆናቸውን ኢጋድ አስታውቋል።
ሽልማቱ በቀጣናው ገንቢ ሚና ያለው ጋዜጠኝነት እንዲጎለብት አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሚዲያ አዋርድ ማስተናገዷም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ስኬቶች ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሚዲያ ሽልማት ውድድሩ ላይ በርካታ የኢጋድ አባል ሀገራት የመገናኛ ብዙሃን ሙያተኞች እንደሚሳተፉም ገልጿል።
የሽልማት ሥነ-ስርዓቱ በአዲስ አበባ መካሄዱም በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ነው ሚኒስቴሩ ያመለከተው።
የኢጋድ የሚዲያ ሽልማት በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ለሚሰሩ የሚዲያ ባለሙያዎች እውቅና ከመስጠት ባለፈ ሙያዊ ደረጃውን የጠበቁ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ዘገባዎች እንዲጠናከሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከር፣ የማህበረሰብን ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ብዝሃ ድምጾች እንዲሰሙ በማድረግ፣ ለዴሞክራሲ እሴቶች መጎልበት እና ዘላቂ ልማት የበኩሉን ሚና ይወጣል።