ቀጥታ፡

በቅሎ ወለደች

ቦንጋ፤ሕዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ዛሬ ከወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ያልተለመደ ክስተት ታይቷል።

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም እንዲሉ ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ በክልሉ ዳውሮ ዞን ዛባ ጋዞ ወረዳ ያማላ ቦካ ቀበሌ አንዲት በቅሎ ወልዳለች።

መውለድ ከማይችሉ እንስሳት ተርታ የምትመደበው በቅሎ የመውለዷ ነገር አዲስ ክስተት ሆኗል።

ጉዳዩን በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የበቅሎዋ ባለቤት የሆኑት አቶ ነጋሽ በተላ በተፈጠረው ነገር እጅጉን መደናገጣቸውን ገልጸዋል።

በቅሎ በተፈጥሮ እንደማትወልድ የሚታወቅ ቢሆንም በቤታቸው የተከሰተውን ነገር ማመን እንደከበዳቸው ነው የተናገሩት።

ከወትሮ የተለየ ነገር እንዳላሳየችና ትላንትና ማታ ባልጠበቁት ሁኔታ ወልዳ መመልከታቸውን አቶ ነጋኝ አውስተው፤ በቅሎዋ ከወለደች በኋላ ምንም አዲስ ነገር እንዳላሳየችም አስረድተዋል።

በዛባ ገዞ ወረዳ የማላ ቦካ ቀበሌ የእንስሳት ባለሙያው አቶ ደረጀ ደስታ ፤ ክስተቱ ከሳይንስና ከተፈጥሮም የሚቃረን ለማመን የሚከብድ መሆኑን ገልጸዋል።

የተወለደው ፍጡር የፈረስ ቅርፅ ያለው ፣ ገና ፀጉር ያላበቀለና ቀኑ ያልደረሰ እንደሆነም አስረድተዋል።

ሲወለድም የሞተ ሲሆን በቅሎዋ አሁን ላይ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሆነችና ምንም የተለየ ምልክት እንዳላሳየችም ነው ለኢዜአ የገለጹት።

ይህን አዲስ ክስተት ከተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የአቶ ነጋኝ ጎረቤት የሆኑት አቶ ባሳ ፈልታሞ፥ይህ ነገር ለማመን የሚከብድ ክስተት ነው፤ ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ነገር ሰምቼም ሆነ አይቼም አላውቅም ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም