ቀጥታ፡

የአፍሪካን ሰላም፣ አንድነትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የሕገ መንግሥታዊ ስርዓትና ውጤታማ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካን ሰላም፣ አንድነትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የሕገ መንግሥታዊ ስርዓትና ውጤታማ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለፁ።

4ኛው የአፍሪካ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዝየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በመክፈቻ ንግግራቸው ሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ህግ ከማውጣት ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን የህግ የበላይነትን ለማስከበር፣ ተጠያቂነትን ለማስፈንና መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሕገ መንግሥት የፖለቲካ ስልጣንን በኃላፊነት መወጣት የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።


 

አፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ አስተዳደርን ለማስፈን የምታደርገው ጥረት የተለያዩ ተግዳሮቶች እየጋጠሙት እንደሚገኝም አንስተዋል።

ስልጣንን በሕገ መንግሥታዊ ስርዓትና በህዝብ ድምፅ ከማግኘት ይልቅ በመፈንቅለ መንግሥትና በተቃውሞ የማግኘት ዝንባሌ በአህጉሪቱ ከሚገጥሙ ችግሮች መካከል መሆኑን ተናግረዋል።

የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ተቋማዊ አቅም ማነስና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን ያልተከተለ ስልጣን የማግኘት ፍላጎት ለአህጉሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ጉዞ ፈተና የሆኑ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የተለየ ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው በንጉሳዊ ስርዓት የነበረው የፍትሐ-ነገሥት እንዲሁም እንደገዳ ስርዓት ያሉ ሀገር በቀል የሕግና አስተዳደር ስርዓቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።


 

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሕገ መንግሥት ያላት ሀገር መሆኗንም ነው ያነሱት።

ሰላምና ብልፅግናዋ የተረጋገጠ የምንመኛትን አፍሪካ ለመፍጠር ፍትሃዊና በቅንነት የሚያገለግሉ የመንግሥት ተቋማትን መገንባት እንደሚገባ በአፅንኦት ጠቅሰዋል።

ለዚህም የሕገ መንግሥታዊ ስርዓት ግንባታ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው የስነዜጋ ትምህርትንና የዳኝነት ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአህጉሪቱን ሰላም፣ አንድነትና ብልፅግና ለማረጋገጥ የሕገ መንግሥታዊ ስርዓትና ውጤታማ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም