የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽነት በማሳደግ አምራች ዜጋን ለማፍራት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽነት በማሳደግ አምራች ዜጋን ለማፍራት እየተሰራ ነው
ባህርዳር ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽነት በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለፁ።
የክልሉ ጤና ቢሮ በየደረጃው ለሚገኘው አመራርና የዘርፉ ተዋናዮች ያዘጋጀው ክልላዊ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ተካሄዷል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለፁት፤ በክልሉ ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ ይገባል።
እስካሁን በተከናወነው ተግባርም ተደራሽነቱን በየጊዜው በማሳደግ የእርስ በእርስ መደጋገፍና መረዳዳት ባህሉን በማጎልበት የጤናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ በሚያዋጣው መጠነኛ ገንዘብ የጤና እክል ሲገጥመው ከነቤተሰቡ ዓመቱን ሙሉ የሚታከምበት ስርአት መሆኑ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በየደረጃው ያለው አመራርም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ሽፋንን ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ ለማድረግ መረባረብ እንዳለበትም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዷለም በበኩላቸው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ1 ሺህ 195 ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት እየተተገበረ ነው ብለዋል።
በአገልግሎቱም ከ63 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ስርዓት የመረዳዳትና የመተጋገዝ መርህ ላይ መመስረቱ በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ጤና አገልግሎት ዋስትና መስጠት እንደሚያስችል አብራርተዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በበኩላቸው፤ በክልሉ ዘላቂነት ያለውና የማይበገር የጤና አገልግሎት ስርዓት ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉም ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ አባዎራዎችና እማዎራዎች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባልነት ታቅፈው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ተመላክቷል።
የህክምና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻልና የመድኃኒት አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ 63 የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች አገልግሎት መስጠታቸውን የመርሀ ግብሩ ተቀባይነት እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።
አመራሩ ከመጪው ታህሳስ 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሚከናወነው የነባር አባላት መታወቂያ ዕድሳትና አዲስ አባላትን የማፍራት ተግባር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣም አሳስበዋል።
በንቅናቄ መድረኩም የክልል፣ የዞንና የወረዳ እንዲሁም የጤናው ሴክተር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።