ቀጥታ፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን የማስፋት ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ነው

አዳማ ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን የማስፋት ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ትምህርት ቤቶችን ከማስፋፋትና ጥራትን ከማስጠበቅ አንፃር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተ ኢዜአ የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ለማን አነጋግሯል።

ኃላፊውም በማብራሪያቸው በገጠርም ይሁን በከተሞች የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የሕፃናት ትምህርትን ባካተተ መልኩ ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት በመሰራቱም በተለይም በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሕፃናት የተሻለ የትምህርት እድል እንዲያገኙ አድርጓል ብለዋል።


 

በዞኑ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት ባለፉት አራት ዓመታት በህብረተሰቡና በመንግሥት ርብርብ 2 ቢሊዮን ብር ሀብት በማሰባሰብ በ11 ወረዳዎች እና በሁለት ከተሞች 571  ቅድመ መደበኛ (ቡኡረ ቦሩ) ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በእነዚሁ ትምህርት ቤቶች ከ70 ሺህ በላይ ህጻናት በአቅራቢያቸው የትምህርት እድል ማግኘት ያስቻላቸው መሆኑን አንስተው በዘንድሮው በጀት ዓመትም ግንባታቸው ከተጀመሩ 107 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መካከል እስካሁን 44   ያህሉ ተጠናቀው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።


 

ለትምህርት ቤቶቹ የንጹህ መጠጥ ውሃ እና በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት በመዘርጋት ለመማር ማስተማሩ ስራ ምቹ መደላድል መፈጠሩንም አስታውቀዋል።

ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበርም በቅድመ መደበኛ የትምህርት ሥርዓት የሰለጠኑ መምህራን ቅጥር ተከናውኖ በየትምህርት ቤቶቹ መመደባቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በሂደት ላይ የሚገኙት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ከ13 ሺህ በላይ ህጻናትን በአቅራቢያቸው ማስተማር የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም