ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን ለበጋ መስኖ ልማት አስፈላጊ የግብርና ግብአቶች ቀርበዋል

ገንዳ ውኃ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ ለበጋ መስኖ ልማት የሚያስፈልጉ የግብርና ግብአቶችን በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን የሕብረት ሥራ ማህበራት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የመተማ ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየን ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የአፈር ማዳበሪያ ለመስኖ ልማቱ እያቀረበ መሆኑም ተመሏክቷል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ ሲሳይ አለበል እንደገለጹት፣ ዞኑ ለመስኖ ልማት የሚውል ሰፊ መሬት፣ ለበጋ መስኖ ልማት የሚስማማ የአየር ንብረትና ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ባለቤት ነው።

በመሆኑም ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለበጋ መስኖ ልማት አስፈላጊ ግብአቶችን በማቅረብ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በልማቱም የአርሶ አደሩን ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመረው የግብአት አቅርቦት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመስኖ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች በየዓመቱ የግብዓት እጥረት ይገጥማቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ዘንድሮ ችግሩን ለመፍታት በተደረገው ጥረት ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ ፀረ ተባይና ኬሚካል ቀድሞ መቅረቡን አቶ ሲሳይ ተናግረዋል።

በመተማ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየን የቀረበው ማዳበሪያም በበጋ መስኖ ልማት የሚሳተፉ አርሶ አደሮችን ምርታማነት በማሳደግ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት የሚያስችል ነው።

የመተማ ገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየኑ ሥራ አስኪያጅ ሀብቴ ዘውዱ በበኩላቸው የበጋ መስኖ ልማትን በግብአት በመደገፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ለዚህም በተያዘው የበጋ ወቅት ለሚካሄደው የመስኖ ልማት ዩኒየኑ 2ሺህ 800 ኩንታል ዳፕ እና ዩሪያ ማዳበሪያ ማቅረቡን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በገንዳውኃ ከተማ ዙሪያ በመስኖ ልማት የተሰማሩት አርሶ አደር አብዱ ሁሴን እንደገለጹት በልማቱ በየዓመቱ ይገጥማቸው የነበረው የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት መፈታቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም