ኮሌጁ የገጠሩን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሌጁ የገጠሩን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ ነው
ድሬደዋ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦የገጠሩን ማህበረሰብ ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት በተቀናጀ መንገድ እየሰራ መሆኑን በድሬዳዋ አስተዳደር የኢትዮ ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ገለጸ።
ኮሌጁ በታዳሽ ኃይል ልማት ከሚሰራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በማህበር ለተደራጁ የገጠር ወጣቶች በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የእህል ወፍጮ አስረክቦ ወደ ስራ አስገብቷል።
የኢትዮ -ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ታደለ አሰፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ወጣቱ የአካባቢውን ፀጋዎች አልምቶ እራሱንና አካባቢውን እንዲለውጥ በክህሎት የታገዘ የተለያዩ ስልጠናዎች ተዳራሽ እያደረገ ይገኛል።
በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ለ120 ወጣቶች ክህሎት መር ስልጠና መስጠቱን ጠቅሰው በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የዘመናዊ ወፍጮ ባለቤት የተደረጉት የቃልቻ ገጠር ቀበሌ ወጣቶች የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት በተገኘ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የተገዛውንና በፀሐይ ሐይል የሚሰራ ወፍጮ በአይነትና በጥራት በኮሌጁ ሰርቶ ማሳያዎች (ወርክሾፖች) በማባዛት በገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የገጠሩን ህብረተሰብ ማህበራዊ ችግሮች የሚፈቱትንና በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ወፍጮዎችን ለማባዛት በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ከሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በገጠር ቀበሌዎች ለሚገኙ ወጣቶች የተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት በፈጠራ እና በክህሎት ታግዘው የአካባቢያቸውን ሃብቶች ወደ ጥቅም እንዲለውጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በኤሌክትሪክ መሳሪያዎች መገጣጠምና መጠገን ስልጠና የተሰጣቸው በማህበር የተደራጁ ወጣቶች በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኮሌጁ የገጠሩን ማህበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ የሚገኘው ስራ የሚበረታታ ነው።
የማህበሩ አባል ወጣት ጀማል ኢብራሂም እንደተናገረው ፤ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ወፍጮ ከበቂ ስልጠና ጋር ማግኘታቸው ቀጣዩን የህይወቸውን ምዕራፍ ለመምራት ያስችላቸዋል።
ይህን መሰል የተቀናጀ ድጋፍ ለወጣቶች ቢደረግ የወጣቱን ተስፋና ህይወት የበለጠ ለመለወጥ እንደሚያስችልም ነው የተናገረው።
የማህበሩ አባል ወይዘሮ ሩሚያ መሐመድ በበኩሏ፤ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰራው ወፍጮ 24 ሰአታት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት የነበረውን ችግር ለመፍታት እንደሚያስችልም ገልጻለች ።
እናቶች በውሃ እና በኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያት ይደርስባቸው የነበረውን ጫና ለመቀነስ ያግዛል ስትል ገልጻለች።