መስኖን ተጠቅመን ባለማነው አትክልትና ፍራፍሬ ተጠቃሚ ሆነናል-አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
መስኖን ተጠቅመን ባለማነው አትክልትና ፍራፍሬ ተጠቃሚ ሆነናል-አርሶ አደሮች
ገንዳውኃ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦ የበጋ መስኖን በመጠቀም ባለሙት አትክልትና ፍራፍሬ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን በልማቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው አርሶ አደሮች እንደገለፁት፤ መስኖን በመጠቀም ባለሙት አትክልትና ፍራፍሬ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን አሳድገዋል።
የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪው አርሶ አደር አደም ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት መስኖን በመጠቀም ቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ።
ባለፉት ቅርብ ዓመታት ያለሙት የማንጎ፣ የፓፓያ፣ የዘይቱን፣ የሙዝ፣ የሎሚና የሌሎች የፍራፍሬ ዝርያዎች ምርት መስጠት በመጀመራቸው ባለፈው ዓመት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በዘንድሮ ዓመትም ካለፈው የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው ከሚያገኙት ገቢም በባንክ በመቆጠብ በቀጣይ ወደ ተሻለ ኢንቨስትመንት ለመግባት ፍላጎቱ እንዳላቸውም አስረድተዋል።
ሌላኛው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሀመድ ገደፋው በበኩላቸው፤ የፍራፍሬ ልማት በቅርብ ጊዜ የተጀመረ ቢሆንም የሚሰጠውን ጥቅም በመረዳት በብዛት የማልማት ስራ እየሰራሁ ነው ብለዋል።
በሩብ ሄክታር ማሳቸው ላይ ባለሙት ፍራፍሬ በዓመት ከ150 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙ መሆኑን ጠቁመው የፍራፍሬ ልማቱን ወደ አንድ ሄክታር ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ቋሚ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት አዋጭ መሆኑን በመገንዘብ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ በዘርፉ መሰማራቱን የገለፀው ደግሞ የመተማ ዮሃንስ ከተማ ነዋሪ የሆነው ወጣት ሰውበሰው አለነ ነው።
ከሁለት ሄክታር በላይ መሬት ላይ ያለማው የማንጎ፣ የፓፓያ፣ የሎሚ፣ የብርቱካንና የዘይቱን ተክል ምርት መስጠት በመጀመሩ እስካሁን ያወጣውን ወጪ በዘንድሮው የምርት ሽያጭ እንደሚመልስም ተስፋ አድርጓል።
በምእራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ አስናቀው አራጋው እንዳሉት፤ በዞኑ አንድ ሺህ 200 ሄክታር መሬት በፍራፍሬና ቋሚ አትክልት ለምቷል።
በዚህም 35 አርሶ አደሮችንና ባለሃብቶችን በማሳተፍ በተካሄደው የፍራፍሬ ልማት ባለፈው ዓመት ከ170 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ የፍራፍሬ ምርት ለገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
እየተገኘ ያለውን ጥቅም በቀጣይ ለማስፋትም ዘንድሮ ከ250 ሺህ በላይ አዳዲስና ቋሚ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ፍል የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተጨማሪም በዞኑ የሚካሄደው የፍራፍሬ ልማት ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠሪያ ዋና አማራጭ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
አርሶ አደሮች የሚፈልጉትን የፍራፍሬ ችግኝ በቀበሌና በወረዳ ማዕከላት ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።