ቀጥታ፡

"ልወቅሽ ኢትዮጵያ" ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን እያጎለበተ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2018(ኢዜአ)፦ "ልወቅሽ ኢትዮጵያ" የተሰኘው ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማነቃቃት በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር የፕሮሞሽን ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተሾመ ተክሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ልወቅሽ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ትውልዱ ስለ ሀገሩ ባህል፣ ታሪክ እና የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲያውቅ ለማድረግ ያለመ ንቅናቄ ነው።

ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በተለያዩ ከተሞች የ"ልወቅሽ ኢትዮጵያ" የሩጫ ውድድር ባለፉት ዓመታት እየተካሄደ እንደሚገኝ ለአብነት አንስተው ፕሮግራሙ በሀገር ውስጥ ቱሪዝም ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ ከሩጫው ባሻገር ልዩ የጉብኝት ፓኬጆችን በማዘጋጀት ዜጎች የተፈጥሮና የቅርስ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በሩጫው ወቅት በሚያልፏባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን እንዲገነዘቡ እያስቻለ መሆኑንም ጨምረው አስታውቀዋል።

ውድድሩ በሚካሄድባቸው ከተሞች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከቱሪዝም ፍሰቱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ዕድል እየፈጠረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከተሞቹ ልዩ ባህሪያቸውንና መስህቦቻቸውን ለብዙኀኑ በማስተዋወቅ የተሻለ ዕውቅና እያገኙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ይህ የስፖርትና የቱሪዝም ትስስር የሀገር ውስጥ እንቅስቃሴን ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ለሀገራዊ ብልጽግና የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዳግም ተሾመ ፕሮግራሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱንና በአሁኑ ጊዜ በስድስት ከተሞች እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ውድድሩ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንዲሁም የውጭ ዜጎች እየተሳተፉበት እንደሚገኙ አንስተው በርካታ ሰዎች በመርሃ ግብሩ ለማሳተፍ ፍላጎታቸውን እያሳዩ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡

መርሀ ግብሩን በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ለማስፋት ዕቅድ መያዙንና ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን በደንብ እንዲያውቁ የቱሪዝም ሀብቶችን እንዲጎበኙ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የዘንድሮው ልወቅሽ ኢትዮጵያ የሩጫ ውድድር ከጥር ጀምሮ በደብረብርሃን፣ ሀዋሳ፣ ጅማ፣ በቆጂ፣ አርባምንጭ፣ ሀረር ዲስከቨር ኢትዮጵያ ክላሲክ በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም