ቀጥታ፡

በተደረገልን ድጋፍ ከተረጅነት ወደ አምራችነት ተሸጋግረናል

ሰቆጣ፤ ሕዳር 19/2018(ኢዜአ)፡ - በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ታቅፈው  የተደረገላቸው ድጋፍ  በመጠቀም ከተረጅነት ወደ አምራችነት  መሸጋገራቸውን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር  የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ገለጹ። 

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በተደረገላቸው ድጋፍ ውጤታማ የሆኑ ከ52 ሺህ  በላይ  ሰዎች  ከተረጅነት መላቀቃቸውን የአስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። 

 አርሶ አደር ሞገስ ቸኮለ በብሔረሰብ አስተዳደሩ አበርገሌ ወረዳ የ01 ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ላለፉት 15 ዓመታት በምግብ ዋስትና ፕሮግራም  ታቅፈው የምግብ እህል ድጋፍ ሲደረግላቸው መቆየቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።


 

ይህም  የዕለት ምግብ ከመሸፈን ባሻገር  ጥሪት  ማፍራት እንዳላስቻላቸው አውስተው፤ በቅርቡ  የውሃ መሳቢያ ሞተር ድጋፍ ተደርጎላቸው አንድ ሄክታር መሬታቸው ላይ የበጋ መስኖን በመጠቀም ሽንኩርት በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ታቅፈው  ላለፉት 10 ዓመታት   ድጋፍ  ሲደርግላቸው እንደቆየ በማስታወስ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ ሌላው የዚሁ ወረዳ  አርሶ አደር  ሃይሌ ጎንጠ ናቸው።


 

መንግስት በገነባላቸው አነስተኛ ግድብና የተደረገላቸውን የውሃ መሳቢያ ሞተር ድጋፍ በመጠቀም በግማሽ ሄክታር መሬታቸው ላይ ቲማቲምና ሽንኩርት በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን   ተናግረዋል።

መንግስት አርሶ አደሩ በምግብ ራሱን እንዲችል እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል  እንዳለበትም አመልክተዋል።


 

በዘላቂነት እራሳቸውን ለመቻልም   በየተሰማሩበት የልማት  ዘርፍ  ተግተው  እየሰሩ መሆኑን   የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ገልጸዋል። 

የአበርገሌ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ መሰረት ወልደየስ ፤  ከሁለት ሺህ በላይ  የፕሮግራሙ   ተጠቃሚዎችን ከተረጅነት ለማላቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከተረጅነት ለማላቀቅ የተያዘውን ግብ ለማሳካትም 78 ሚሊየን ብር የቀጥታ ድጋፍ ተደርጓል ያሉት ወይዘሮ መሰረት፤  ለ200 ተጠቃሚዎችም የውሃ መሳቢያ ሞተር ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል።


 

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የምግብ ዋስትና ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ  ገብረኪዳን እንደገለጹት ፤ በአስተዳደሩ በፕሮግራሙ  የታቀፉ ተጠቃሚዎችን ከተረጅነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር የገንዘብ  ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል።


 

በተደረገላቸው ድጋፍ በእንስሳት እርባታ፣ በንግድና በመስኖ ልማት ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ ከ52 ሺህ በላይ ሰዎችን  ከተረጅነት ማላቀቅ ተችሏል ብለዋል።

ቀሪዎቹን  በዘላቂነት  ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገርም በ20 ሚሊየን ብር አምስት የመስኖ መሰረተ ልማቶች በብሔረሰብ አስተዳደሩ በመገንባት ላይ እንደሚገኙም  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም