ምርቶችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምርቶችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው
ደብረብርሃን ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ሃላፊ ተወካይ ፈጠነ ሞገስ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመንግስት ለገበያ ማረጋጋት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
ባለፉት አራት ወራት ብቻ በሸማቾች ሕብረት ሥራ ማህበራት በኩል 429 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ገበያ የማረጋጋት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም 141 ሺህ ኩንታል ጤፍ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ሌሎች የግብርና ምርቶች እንዲሁም 38 ሺህ ኩንታል የኢንዱስትር ውጤቶችን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከ425 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት መቅረቡን ጠቁመው በቀጣይም ምርቶችን ለሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የመንግስት ሠራተኞች በሦስት ወር ክፍያ የሚፈልጉትን ምርት ወስደው እንዲጠቀሙ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም አስረድተዋል።
ከምርት አቅርቦት በተጨማሪ ያለአግባብ ምርት በሚደብቁና ዋጋ በሚጨምሩ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጎለላና ጠራ ወረዳ የመንግስት ሠራተኞች ሸማች ህብረት ሥራ ማህበር ፀሀፊ አቶ አስፋው ንጋቱ እንደገለጹት፤ ማህበሩ 15 ሚሊዮን ብር በመመደብ 215 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና ስኳር አቅርቧል።
በቅርቡ የበርበሬ ምርት ለማቅረብ ከአምራች አርሶ አደሮች ጋር የግዥ ውል መፈፀሙንም ጠቁመዋል።
ከተጠቃሚዎች መካከልም አቶ ልዑል ታደሰ ፤በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል የሚቀርቡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በማህበራት ስኳር በገበያ ካለው ዋጋ በኪሎ እስከ 40 ብር፣ የዳቦ ዱቄት እስከ 20 ብር ቅናሽ እንዲሁም ሌሎች ምርቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበላቸው መሆኑን ተናግረዋል።