አርሶ አደሮች በመስኖ ያለሙትን የጓሮ አትክልት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሮች በመስኖ ያለሙትን የጓሮ አትክልት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል
ሀዋሳ ፤ ሕዳር 19/2018 (ኢዜአ)፦በመስኖ ያለሙትን የጓሮ አትክልት ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገጠር ቀበሌ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የበጋ መስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች እንዳሉት፤ በሽንኩርት፣ በርበሬ፣ ቲማቲም፣ ጎመንና ሌሎች የጓሮ አትክልቶች ካለሙት ማሳ በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት ያገኛሉ።
አርሶ አደሮቹ በከተማ አስተዳደሩ ቱላ ክፍለ ከተማ ፊንጫዋ ቀበሌ በኩታ ገጠም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን እያለሙ ይገኛሉ።
ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ዳዊት ዶጊሶ፤ ዘንድሮ ከክፍለ ከተማው እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት በተደረገላቸው ድጋፍ ከአትክልት በተጨማሪ በርበሬ ለመጀመሪያ ጊዜ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በየዓመቱ በመስኖ ልማት ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ጥቅል ጎመን አልምተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙና ከቤት ውስጥ ፍጆታ ያለፈውን በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለመስኖ ልማት ሥራቸው ከጉድጓድ ውሀ ለሚስቡበት ሞተር ነዳጅ በቅርበት አለማግኘት ለስራቸው እንቅፋት በመሆኑ መፍትሄ እንዲገኝላቸው ጠይቀዋል።
ሌላው የመስኖ ልማቱ ተሳታፊ አርሶ አደር ተስፋዬ ዶጊሶ በበኩላቸው፤ ጥቅል ጎመን፣ ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲምና በርበሬ በኩታ ገጠም እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በፊንጫዋ ቀበሌ በተለያዩ ቀጣናዎች ያላቸውን መሬት በበጋ መስኖ በማልማት በየዓመቱ ከሚሰበስቡት ምርት ገቢያቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
አምና ከሽንኩርትና ጥቅል ጎመን ሽያጭ 150 ሺህ ብር ማግኘታቸውን ያስታወሱት አርሶ አደሩ፣ ዘንድሮ ከሽንኩርትና ጥቅል ጎመን በተጨማሪ በርበሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ማልማታቸውን ጠቁመዋል።
“በርበሬ በገበያ ያለው ዋጋ እየጨመረ ስለመጣ የተሻለ ገቢ አገኝበታለሁ በሚል በግብርና ባለሙያ ድጋፍ ታግዤ አልምቻለሁ፤ በማሳው ላይ ያለው ይዞታም ጥሩ ነው።" ብለዋል።
በቱላ ክፍለ ከተማ ፊንጫዋ ቀበሌ የግብርና ባለሙያ አቶ መብሩ መሌ እንዳሉት፤ በቀበሌው 176 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በበጋ መስኖ እየለማ ይገኛል።
በሦስት ክላስተር እየተከናወነ ባለው የበርበሬ፣ ጥቅል ጎመንና ቀይ ሽንኩርት፣ አበሻ ጎመንና ቲማቲም ልማት 405 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በቀበሌው ዘንድሮ በሴፍቲኔት መርሀ ግብር 14 ጥልቅ የውሃ የጉድጓድ መቆፈሩንና በከተማ አስተዳደሩ የውሀ መሳቢያ ሞተሮች መቅረባቸውን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የጓሮ አትክልቶች ከለማው ማሳ እስከ 10 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጋና ኔቶ እንዳሉት፤ በቱላ ክፍለ ከተማ ቱሎ፣ ፊንጫዋ፣ ጋራ ሪቀታና ዳቶ ቀበሌዎቸ 2 ሺህ 205 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እየለማ ነው።
በዚህም ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ጥቅል ጎመንና ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በሀዋሳ ከተማ ያለውን ገበያ የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመስኖ ልማቱ 1ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር በመስኖ ከለማው ማሳም እስከ 80 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።